AMN – የካቲት 12/2017 ዓ.ም
በግማሽ ዓመቱ በአንደኛው እና ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ከ70 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩን በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ እና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ ገልጸዋል፡፡
አቶ ጥራቱ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች የስራ ዕድል እንዲያገኙ በስፋት እና በንቅናቄ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በዚህም ከተማ አስተዳደሩ ለስራ ዕድል ፈጠራ ልዩ ትኩረት በመስጠቱ ተቋም በማደራጀት’ የሰው ኃይል እና በጀት በመመደብ በትኩረት እየሰራበት መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ አመራርም ለዚህ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነውም ብለዋል፡፡
ባለፉት 6 ወራት 142 ሺህ 908 ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው መሆኑን ያወሱት አቶ ጥራቱ፣ ይህም የእቅዱ 95 በመቶ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተለይም ለወጣቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት ከአጠቃላዩ የስራ እድል 70 በመቶ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ እየተሰራም ነው ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል የስራ አጥ ምዝገባ ይከናወን የነበረው በማኑዋል ነበር ያሉት ኃላፊው ይህም ትክክለኛ መረጃን ለመያዝ አስቸጋሪ በመሆኑ ከዚህ ዓመት ጀምሮ በሁሉም ወረዳዎች ስራ ፈላጊዎችን በሲስተም መመዝገብ መጀመሩን አውስተዋል፡፡
የስራ አጥ ምዝገባው በአሻራ ጭምር እየተከናወነ ነውም ብለዋል፡፡
ይህም ግልጸኝነትን እና ፍትሀዊነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን አውስተዋል፡፡
ከዚህም ሌላ በየአንዳንዱ ብሎክ ስራ ፈላጊዎችን በመለየት የመመዝገብ ስርዓት ተዘርግቶ እየተሰራበት መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ከዩንቨርሲቲ ተመርቀው የሚወጡ ተመራቂዎች የስራ ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ 20 ሺህ 299 ተመራቂዎች ከአጠቃላይ የስራ እድል ፈጠራ 14 በመቶውን ተጠቃሚ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡
13 ሺህ 731 የሚሆኑ ወጣት ስራ ፈላጊዎች በግል ድርጅቶች የስራ ልምምድ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ያወሱት አቶ ጥራቱ ከእነዚህም ውስጥ 99 በመቶ የሚሆኑት ልምምድ ባደረጉባቸው ድርጅቶች የስራ እድል ማግኘታቸውን አመልክተዋል፡፡
የመንግስት የስራ እድል ፈጠራ ብቸኛው የስራ እድል አማራጭ መሆን የለበትም ያሉት አቶ ጥራቱ የግል ድርጅቶች እና ኩባንያዎችም ይህን ስራ ሊጋሩት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የስራ ባህልን ከመቀየር አኳያ በተለይም የኮሪደር ልማት ስራው ይህን የቆየ የስራ ባህል እንደቀየረው ተናግረዋል፡፡
የኮሪደር ልማት ስራው የስራ መነሳሳትን፣ 24 ሰዓት መስራትን እና ስራ ሳያማርጡ የመስራት ባህልን የፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ይህ የስራ ባህል ወደ ሁሉም ሴክተሮች እንዲሰፋ እና ይህም በጥናት እነዲደገፍ እየተደረገ መሆኑን ነው የጠቀሱት፡፡
ስራ ፈጣሪ ኢንተርፕራይዞችን መፍጠር ላይ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ጥራቱ፣ ለዚህም ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለዚህም 160 ሚሊየን ብር ተመድቦ ስራ ፈጣሪ ኢንተርፕራይዞችን የመደገፍ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በዚህም ከ 600 ሺ እስከ 10 ሚሊየን ብር ካፒታል የፈጠሩ 165 ጥቃቅን እና አነስተኛ ወደ ኢንተርፕራይዝነት እንዲሸጋገሩ ዝግጅት መደረጉን አውስተዋል፡፡
ይሁን እና የስራ እድል ፈጠራው በቂ ባለመሆኑ በዚህ ረገድ ተጨማሪ ስራዎችን መስራት እንደሚገባ አቶ ጥራቱ አንስተዋል፡፡
በሰለሞን በቀለ