AMN ሰኔ 12/2017
በወንጀል ድርጊት የተገኘን ንብረት ወይም ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005ን ለማሻሻል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1387/2017 ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁ ይታወቃል።
በተሻሻለው አዋጅ ዙሪያ የህብረተሰቡ ተጨማሪ መረጃን ተደራሽ ለማድረግም የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን አማረ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1387/2017 ከነባር አዋጁ 780/2005 በ58 አንቀጾች 14ቱ ላይ ማሻሻያ አድርጓል ብለዋል።
አዋጁ ሽብርተኝነትንና ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ህጎች ጋር የተጣጣመ መሆኑን ተናግረዋል።
የማሻሻያ አዋጁ በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀል ድርጊትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ዓለም አቀፍ ጥረት ላይ ኢትዮጵያ ድርሻዋን በአግባቡ እንድትወጣ ያስችላል ብለዋል።

አዋጁ አመንጪ የሚባሉ 21 ወንጀሎችን በአባሪነት ያስቀመጠ ብሎም ለትርጉም ተጋላጭ የነበሩ ጉዳዮችን በግልጽ የሚየስቀምጥ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ተገቢ ምርመራ ለማካሄድ እንደሚጠቅምም ገልጸዋል።
በወንጀል ድርጊት የቅጣት አለመመጣጠን መልክ ሊያስይዝ የሚያስችልም ጭምር ነው ብለዋል።
በሽፋን ስር ለሚደረጉ የምርመራ ሂደቶች ወይንም ልዩ የምርመራ ሂደቶች በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብቻ የሚከናወን መሆኑን ማስቀመጡን ተናግረዋል።
ይህም ፍርድ ቤቱ በመደበኛ የምርመራ ዘዴ ማስረጃ ማግኘት አዳገች መሆኑን አምኖ በሰጠው ፈቃድና ትዕዛዝ መሠረት የሚከናወን መሆኑንም ጠቁመዋል።
ይህ የምርመራ ዘዴም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚደረግ መረጃን ለማግኘት በጥብቅ ዲሲፕሊን እና በፍርድ ቤት ቁጥጥር ስር የሚከናወን መሆኑን መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በአጠቃላይም የተሻሻለው አዋጅ የሀገርን ደህንነትና የህዝብን ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆኑንም ጠቁመዋል።