AMN – ታኀሣሥ 25/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እያከናወናቸው ባሉ እና በቀጣይ ሊያከናውናቸው ባቀዳቸው ስራዎች ላይ ከኢፌዴሪ ሚሲዮኖች ጋር ውይይት አካሄዷል።
በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር)፣ ኮሚሽነሮች፣ አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።
በውይይቱ ላይ ኮሚሽኑ ባከናወናቸው ተግባራት፣ ባጋጠሙ ተግዳሮቶች እና በቀጣይም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በውጭ ሀገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በአካል በመገኘት ያላቸውን አጀንዳ እና ጥያቄዎች ለማዳመጥ እና ለማሰባሰብ ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሚሲዮኖች በሚፈልጋቸው ትብብሮች ላይ ገለጻ ቀርቧል።
ሀገራዊ ምክክር ግጭትን በማስወገድ ረገድ ያለው ሚና የላቀ እንደመሆኑ መጠን ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን እና የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ያለው ሚናም ተብራርቷል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ አካታች፣ ነጻ እና ገለልተኛ በመሆን በውጭ ሀገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ እንዲሁም የዳስፖራ አደረጃጀቶች ጋር ምክክር ሲያደረግ መቆየቱ እና ከውይይቶቹም ጠቃሚ ግብአቶችን ማሰባሰብ መቻሉም ተጠቅሷል።
በገለጻው ላይ በመመስረት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሚሲዮን መሪዎች እና ዲፕሎማቶች ጥያቄና አስተያየት ያቀረቡ ሲሆን ኮሚሽነሮች ምላሽ እና ማብራሪያ መስጠታቸውን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡