በዓሉ ከሃይማኖታዊ በዓልነት ባሻገር የሚታይ ለዓለም በማይዳሰስ ቅርስነት የተበረከተ ሀብታችን ነው-የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

You are currently viewing በዓሉ ከሃይማኖታዊ በዓልነት ባሻገር የሚታይ ለዓለም በማይዳሰስ ቅርስነት የተበረከተ ሀብታችን ነው-የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

AMN – ጥር 10/2017 ዓ.ም

የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

ጥምቀት ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው የአደባባይ የወል በዓል ነው ያሉት አገልግሎቱ በዓሉ ከሃይማኖታዊ በዓልነት ባሻገር የሚታይ ለዓለም በማይዳሰስ ቅርስነት የተበረከተ ሀብታችን ነው ሲልም ገልጿል፡፡

የበዓሉ መሠረት ሃይማኖታዊ መሆኑን በመግለጽ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ሃይማኖታዊ መሠረቱን እንደያዘ ባህላዊ እሴት እንዲኖረዉ ጭምር አድርገውታል ተብሏል፡፡

በዓሉ በየዓመቱ ሲከበር ከክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ባሻገር መላው ሕዝብ የሚታደምበት የዐደባባይ የወል በዓል ተደርጓል ብሏል አገልግሎቱ፡፡ ኢትዮጵያ ለዓለም ሕዝብ ያበረከተችው የማይዳሰስ ቅርስ ኾኖ መመዝገቡም ለዚህ ማሳያ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የጥምቀት በዓል ከሌሎች የሃይማኖታዊ በዓላት ለየት የሚያደርገዉ በሃይማኖት ተቋማት ቅጥረ ግቢ ወይም በቤት ውስጥ ብቻ የሚከወን አለመኾኑና ደስታን ለአጠቃላይ ማኅበረሰቡ ማጋራቱ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በሃይማኖታዊ እና ባህላዊ አልባሳት ያጌጡ ምዕመናንና ታዳሚዎች በጋራ የሚያከብሩት ድንቅ በዓል መሆኑም ተገልጿል፡፡

በዓሉ ከሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዐት፣ መዝሙሮች እና ባህላዊ ጭፈራዎች ባሻገር የገና ጨዋታ እና የፈረስ ግልቢያ መሰል ኹነቶች የሚያደምቁት ነው ያለው አገልግሎቱ ይህንን ትውፊቱን የጠበቀ በዓል ጎብኝዎች ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለመታደም ዐቅደዉ ይመጣሉ፤ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ፣ የሕዝቧን አብሮነት እና እንግዳ ተቀባይነት ተመልክተዉበትም ይመለሳሉ ብሏል፡፡

በዚህ በዓል ላይ የወጣቶች ተሳትፎ እና ሚና በእጅጉ ልቆ እንደሚታይ ተመላክቷል፡፡

ታቦታቱን ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ ድረስ በዝማሬ እና ጭፈራ ያጅባሉ፤ የታቦታቱን መንገድ ይጠርጋሉ፤ ምንጣፎችን ያነጥፋሉ፤ ይሸከማሉ፤ በገና ጨዋታና ፈረስ ጉግስ ይሳፋሉ፤ ይህ ጠንካራ ማኅበራዊ እሴት እየዳበረ መጥቷል ነው ያለው አገልግሎቱ በመልዕክቱ፡፡

የጥምቀትንም በዓል ስናከብር ጥንታዊ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ትውፊቱን ጠብቀን፤ የሃይማኖት አባቶች፣ ምዕመናን፣ ወጣቶች እና መላዉ ሕዝባችን የነበረ ሚናችንን እየተወጣን ሊኾን ይገባል ሲል መልዕክት አስተላልፏል፡፡

በዓሉ ደስታን የምንጋራበት የዐደባባይ በዓል ነውና ደስታችንን እየተጋራን ልናከብረው ይገባል ሲልም ገልጿል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review