በዘመቻ መልክ ሲከናወኑ የቆዩ ተግባራት ባህል እስኪሆኑ ድረስ መስራት ይገባል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing በዘመቻ መልክ ሲከናወኑ የቆዩ ተግባራት ባህል እስኪሆኑ ድረስ መስራት ይገባል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN – ጥር 23/2017 ዓ.ም

“ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ በሚገኘው ሁለተኛው የብልፅግና ፓርቲ መደበኛ ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቃል እስከ ባህል ለሚለው ሀሳብ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸውም፣ ሀሳብ በቃል ይነገራል፣ በሰነድ ይሰነዳል፣ በተግባርም ይገለጣል ያሉ ሲሆን፣ ነገር ግን ይህ ሀሳብ በድግግሞሽ በልምምድ ደግሞ ባህል ይሆናል በማለት አብራርተዋል፡፡

ባህል ሲባል ደግሞ ልማድ፣ እሴት ትዕምርት፣ ካለማንም ጎትጓች፣ ካለማንም ቀስቃሽ በራስ ተነሳሽነት የሚከወን ነገር ነው ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በፅዳት፣ በከተማ ግብርና፣ ተፈጥሮን በመንከባከብ የተለያዩ ተግባራትን በሀገር አቀፍ ደረጃ በዘመቻ መልክ ለማከናወን እንደተሞከረ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን እንቅስቃሴ ባህል እስኪሆን ድረስ ደጋግሞ ማከናወን እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት፡፡

ከሁሉ በላይ ደግሞ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የመጨረስ ልምምድ ባህል መሆን እንደሚገባውም አስገንዝበዋል፡፡

ብልፅግና ባህል መፍጠር አለብን ሲል አምስት አንኳር ጉዳዮችን ነቅሶ እንደሚያነሳም ጠቁመዋል፡፡

በዚህም አንደኛው ማወቅ ሲሆን፣ ይህም ሀገርን፣ ህዝቡን፣ ባህሉን፣ ቋንቋውን፣ እሴቱን፣ ስነ ምግባሩን፣ የኢትዮጵያን ፀጋ፣ በቅጡ ጠንቅቆ ማወቅ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

የተለያዩ ክፍሎች ካለማወቅ እና ካለመገንዘብ ኢትዮጵያን እንዳሻቸው ማድረግ የሚችሉ ይመስላቸዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ያ ኢትዮጵያ ዛሬ የለም፣ ዛሬ ያለው ኢትዮጵያ በእኩልነት፣ በዲሞክራሲ፣በመከባበር በወንድማማችነት ስሜት ብቻ ለጋራ ህልም እና ራዕይ የምንሰራበት እንጂ አንዱ ሌላውን ተጭኖ እና ዘርፎ የሚሄድበት ሁኔታ ከእንግዲህ መከወን የሚቻል ተግባር አይደለም ብለዋል፡፡

ሁለተኛው ነጥብ ማላቅ ነው ያሉት ዶክተር ዐቢይ፣ ያለንን፣ የተሰጠንን ፀጋ ማወቅ ብቻ ሳይሆን ማሻሻል ነው፣ ለዚህም ጣና ነበረ ጎርጎራን ጨምሮ ማሳመር፣ ፋሲል ነበረ አሸብርቆ አምሮ እንዲታይ ማድረግ፣ አባ ጂፋር ነበረ ይበልጥ ልቆ እንዲታይ ማድረግ፣ ሀላላ ኬላ ነበር እንዲህ ዓይነት ስፍራ አለ አንዴ እስኪባል ድረስ አልቆ መስራት ነው በማለት አብራርተዋል፡፡

ሌላኛው ነጥብ መፍጠር መሆኑን በማንሳትም፣ መፍጠር ማለት በተለየ መንገድ ማየት፣ በተለምዶ ከምናየው ነገር ባሻገር በአዲስ መልክ በአዲስ መነፅር መመልከት መቻል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ይህም አንድን ነገር ማየት ብቻ ሳይሆን በጭንቅላት ጨርሶ መጀመር ማለት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

ብልፅግና ፓርቲ ባህል መፍጠር አለብን ሲል የሚያነሳው ሌላኛው ነጥብ ደግሞ መፍጠን መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም ጊዜ የለንም በሚል መንፈስ ፈጥኖ መስራት መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ሌላኛው መሠረታዊ ነጥብ ማስተሳሰር ሲሆን፣ ይህም ህዝብን፣ ሀሳብን፣ ውጤትን እና የተለያዩ የተራራቁ ጉዳዮችን ማስተሳሰር ማለት እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review