በዜጎች ላይ እገታና ግድያ በመፈፀም እና የትምህርት ሂደትን በማወክ በመምህራን ላይ በደልና ግፍ እያደረሰ ባለው ፅንፈኛ ቡድን ላይ የተጠናከረ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ ገለጹ።
በአማራ ክልል ያለውን አጠቃላይ የፀጥታ ሁኔታና በፅንፈኛው ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር እርምጃ በተመለከተ የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ እሸቴ የሱፍ(ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በማብራሪያቸውም፥ ሀገር የማፍረስ ዓላማ ይዞ የተነሳው ፅንፈኛ ቡድን በተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ በሰዎች ላይ ግድያ፣ ዘረፋና ውድመት ማስከተሉን አንስተዋል።
ከዚህ ተግባር በመታቀብ ሰላማዊ አማራጭን በመከተል የጥፋት መንገዱን እንዲተው በመንግስት ተደጋጋሚ ጥሪ መቅረቡንና አሁንም የሰላም እጁን እንዳላጠፈ ገልፀዋል።
በዚህም በርካታ ታጣቂዎች የፅንፈኛ ቡድኑን እኩይ አላማ በቅጡ በመረዳትና የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለስ መቻላቸው ይታወቃል።
ከዚህ ውጭ በጥፋት መንገድ በመቀጠል በግድያ፣ ዘረፋና የእገታ ተግባር ላይ በሚገኘው ፅንፈኛ ቡድን ላይ የተቀናጀና የተጠናከረ ህግ የማስከበር እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።