AMN – ጥር 21/2017 ዓ.ም
ሁለተኛው የብልፅግና ፓርቲ ጉባዔ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያረጋግጡ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት እንደሚሆን የፓርቲው የክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊዎች ገለጹ።
ብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤውን “ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ሀሳብ ከጥር 23 እስከ 25 በአዲስ አበባ ያካሂዳል።
ጉባዔውን አስመልክቶ ሃሳባቸውን ያጋሩ የፓርቲው የክልሎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ጉባዔው ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚያሻግሩ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች የሚተላለፉበት መሆኑን ተናግረዋል።
በፓርቲው የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጌቱ ወዬሳ ጉባዔው ኢትዮጵያን ለማሻገር የተያዙትን አቅጣጫዎች የሚያጠናክሩ ውሳኔዎች የሚወስኑበት እንደሚሆን ጠቅሰዋል።
ፓርቲው ባለፉት ዓመታት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በዲፕሎማሲ ዘርፎች ያሳካቸውን ስኬቶች ቀጣይነት ለማረጋገጥ እንደሚመክርም ገልጸዋል።
በፓርቲው የጋምቤላ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አሺኔ አስቲን በበኩላቸው ፓርቲው ባለፉት ዓመታት ክንውኖችና ስኬቶች በጉባኤው እንደሚገመገሙ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ልዕልና የምታደርገውን ጉዞ የሚያሳኩ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡም እንዲሁ።
ፓርቲው በመጀመሪያው ጉባኤ የተላለፉ ውሳኔዎችን አፈጻጸም በመገምገም የህዝብን አንገብጋቢ ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችሉ ውሳኔዎችም እንደሚያሳልፍ የገለጹት በፓርቲው የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አብርሃም ማርሻሎ ናቸው።
በብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ(ዶ/ር) ከጉባኤው ለጠንካራ ተቋማዊ ግንባታ መደላድል የሚፈጥሩ ውሳኔዎች ይጠበቃሉ ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሰላምና የልማት ጉዳዮች የሚያፋጥኑ እና ሁለንተናዊ ብልጽግናን የሚያፋጥኑ ውሳኔዎች እንደሚወሰኑ ይጠበቃል ብለዋል።
ፓርቲው ህብረብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ያከናወናቸውን ውጤታማ ስራዎች የሚያጎለብቱ አቅጣጫዎች ላይ በጉባዔው መግባባት ላይ እንደሚደረስ በፓርቲው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢሳቅ አብዱልቃድር ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ ውጥንን ይበልጥ ስኬታማ የሚያደርጉ አቅጣጫዎች እና ውሳኔዎች እንደሚተላለፉበት መግለጻቸው ይታወቃል።