በጊምቢ ከተማ ለሚገነባው ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የግንባታ ማስጀመሪያ መሠረት ድንጋይ ተቀመጠ

You are currently viewing በጊምቢ ከተማ ለሚገነባው ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የግንባታ ማስጀመሪያ መሠረት ድንጋይ ተቀመጠ

AMN – የካቲት 27/2017 ዓ.ም

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ከተማ ለሚገነባው ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የግንባታ ማስጀመሪያ መሠረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡

የግንባታ ማስጀመሪያውን የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) መሆናቸውም ተመላክቷል፡፡

ሚኒስትሩ፣ በዚህ ወቅትም ባደረጉት ንግግር፣ የኢትዮጵያን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል እየተወሰዱ ካሉ እርምጃዎች ውስጥ አንዱ የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት ማሻሻል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መሠረተ ልማት የተሟላላቸው ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለመገንባት እየተሠራ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ ይህ ዛሬ የግንባታ ማስጀመሪያ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዚሁ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

የትምህርት ቤቱ ግንባታም በአጭር ጊዜ ተጠናቆ የመማር ማስተማር ስራውን እንዲጀምር ይደረጋልም ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ደረጃቸው የተሻሻሉና መሠረተ ልማት የተሟላላቸው ትምህርት ቤቶችን መገንባት ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።

የዞኑ አመራሮች በበኩላቸው፣ በትምህርት ቤቱ ግንባታ መጀመር ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው፣ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮሬሰር ብርሃኑ ነጋ እና ሌሎች አመራሮች በጊምቢ ከተማ በሚገኙት ቢፍቱ ጊምቢ እና ሴና ጊምቢ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመገኘት ያለውን የመማር ማስተማር ሂደት በመመልከት ተማሪዎችን ማበረታታቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review