AMN- ጥቅምት 21/2017 ዓ.ም
በግብርናው ዘርፍ 6 ነጥብ 6 በመቶ እድገት ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
6ኛው የህዝተወካዮች ምክር ቤት ብ 4ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ስብሰባ እየተካሄደ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጡ ነው፡፡
የግብርና መሰረተ ልማት እየሰፋ በመሄዱ የሚጠበቀው እድገት እውን እንደሚሆን አስገንዝበዋል፡፡
በተለይም በሰብል፣ በጥጥት እና በሆልቲካልቸር ምርት 30 ሚሊየን ሄክታር መሬት መታረሱን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም 15 ሚሊየን ሄክታር ይታረስ እንደነበር እና አሁን የሚታረሰው መሬት በእጥፍ ማደጉን አውስተዋል፡፡
የበጋ እርሻ ስራው በተለይም በኩታ ገጠም እና በመስኖ ልማት እንደሚከናወን እና በዚህም በግብርናው ዘርፍ የ6 ነጥብ 6 እድገት እንደሚመዘገብ አስረድተዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በግብርናው ዘርፍ 6 ነጥብ 1 በመቶ መመዝገቡን አንስተዋል፡፡
የሌማት ትሩፋትን በተመለከተ በዚህ ዓመት በወተት ልማት 12 ቢሊየን ሊትር ወተት ፣218 ሺ ቶን የዶሮ ስጋ ፣8 ቢሊየን እንቁላል ፣297 ሺ ቶን ማር ፣2 ነጥብ 28 ሺ ቶን የዓሳ ምርት በአጠቃላይ በሌማት ትሩፋት 5 ነጥብ 4 በመቶ እድገት እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
በደን ልማት፣ በአትክልት እና ፍራፍሬም ትልቅ ስራ እየተሰራ እንደሆነና በዚህ ረገድም ትልቅ እድገት እንደሚመዘገብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
በተለይም በቡና ባለፈው ዓመት 1 ሚሊየን ኩንታል ምርት መገኘቱን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እድገቱን በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር ኢትዮጵያ ከብራዚል እና ቬትናም ቀጥሎ 3ኛዋ ቡና አምራች አገር እየሆነች መሆኑን አውስተዋል፡፡
በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ደግሞ ከብራዚል ቀጥላ ትልቋ ቡና አምራች አገር እንደምትሆን ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ በቡና የተገኘውን 1ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር በቀጣይ 2 ቢሊየን ዶላር ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዚህም ከ450 እስከ 500 ሺ ቶን ቡና ምርት ለውጭ ገበያ እንደሚቀርብም ገልጸዋል፡፡
በሻይ ቅጠል ምርት በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ እየተመረተ እንደሚገን እና በዚህም ውጤት መገኘቱን አውስተዋል፡፤ አሁን ካለው ምርት በ3 እጥፍ ለማምረት እየተሰራ ነውም ብለዋል፡፡
ምርቱን በማሳደግ 20 የሻይ ቅጠልማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ለመትክል ከባለሀብቶች ስምምነት መደረሱንም አውስተዋል፡፡
የስንዴ ምርትን አስመልክቶ በሰጡት ማብራያ ከ8 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት መታሱን ገልጸዋል፡፡
በሄክታር 40 ኩንታል ስንዴ ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በዚህም 30 ሺ ቶን ወይም 300 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ለማምረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሰሊጥ ፣ለውዝ እና አኩሪ አተር እንዲሁም ቦሎቄ ከዚህ ቀደም ከነበረው ምርት የበለጠ ለማምረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
5 ሺ ሄክታር መሬት ላይ የለውዝ ምርት እየተመረተ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
በዚህ ዓመት የመሬት ጸባይ ላይ የተመሰረተ ማዳበሪያ የማዘጋጀት ስራ እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጥ ዘርን ማሰራጨትን አስመልክቶ 100 ፐርሰንት እድገት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
መስኖ እና የበጋ ስራ በተመለከተ ፓምፕ እና ማሽነሪ የማሰራጨት ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን አውስተዋል፡፡
በዚህም በዋናነት ጥራት እና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
በሰለሞን በቀለ