በጎነት የስልጣኔ አብነት

You are currently viewing በጎነት የስልጣኔ አብነት

በበጎ ልቦች ሕይዎቴ ጣፍጧል“∫

                                በበጎ ፈቃደኞች ቤታቸው የታደሰላቸው እናት

በይግለጡ ጓዴ

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፅንሰ ሀሳብ እንደየህብረተሰቡ የዕድገት ደረጃና አካባቢያዊ ሁኔታ የሚለያይ በመሆኑ አንድ ወጥ ትርጉም ባይኖረውም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሁሉም ስልጣኔና ማህበረሰብ አካልና ውጤት ነው ይለዋል።

ፅንሰ ሀሳቡ ሲተነተን የበጎ ፈቃድ አስተዋፅዖ በተለያዩ መስኮች እያንዳንዱ ሰው ያለ ትርፍ ፍለጋ፣ ያለ ክፍያ፣ ሙያዊ አጽንዖት ባልተጫነው ሁኔታ ለማያውቋቸው ግለሰቦችና ለሚያውቋቸው ጎረቤቶቹ፣ ለማህበረሰቡና በጠቅላላው ለህዝብ የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ መሆኑን ያመላክታል፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዕድሜና ፆታ፣ ማህበራዊ ደረጃ፣ መልከዓ ምድራዊ ወሰን ሳይገድበው የሰብዓዊነት መርህን ብቻ መሠረት በማድረግ የሚሰጥ ወይም የሚከናወን ተግባር ነው፡፡ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አስፈላጊ የሆነባቸው መሠረታዊ ነጥቦች በርከት ያሉ ቢሆኑም ዋና ዋናዎች ግን የሚከተሉት ናቸው፡፡ ወጣቱ የማህበረሰቡን መልካም ዕሴቶች እንዲቀስም ለማስቻል፣ የወጣቱን ማህበራዊ ተሳትፎ ለማበረታታትና ለማሳደግ የወጣቱን ዕምቅ አቅም ለመጠቀም፣ ለህፃናትና ለታዳጊ ወጣቶች አርዓያ (ሞዴል) የሚሆን ወጣት ትውልድ ለማፍራት ነው፡፡

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ እቴነሽ ተክለዮሐንስ ምንም አጋዥና ረዳት የሌላቸው እማወራ ናቸው፡፡ ቤታቸው በክረምት ዝናብ የሚያፈስና በበጋ ደግሞ ፀሐይ ሲፈራረቅበት እንደነበር ጠቁመዋል። ቤቱ ስሙ ቤት ይባል እንጂ ከዝናብና ፀሐይ የማይከላከልላቸው ቤት እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በክረምቱ ዝናብ ምክንያት የቤት እቃቸው ሙሉ በሙሉ እንደተበላሸባቸው ገልጸዋል፡፡ የቤት እቃ ገዝተው የሚተኩበት ገንዘብ የሌላቸው ችግረኛ መሆናቸው ደግሞ ኑሯቸውን ይበልጥ አክብዶባቸው ነበር፡፡

የአካባቢው በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ የወረዳው የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት እና የአካባቢው በጎ ፈቃደኛ ባለሃብቶች ችግራቸውን ተመልክተው ቤታቸውን አፍርሰው እንደገና ሰርተውላቸዋል። ወ/ሮ እቴነሽ አሁን በሞቀ ቤት ውስጥ ይኖራሉ፡፡ እንደወትሮው ዝናብና ፀሐይ አያገኛቸውም፡፡

ለዚህም ለፈጣሪያቸው እና ለበጎ ፈቃደኛ የህብረተሰብ ክፍሎች ምስጋናቸውን የሚያቀርቡት ወ/ሮ እቴነሽ በሙቀት ቤታቸው ሆነው ቀሪ ዘመናቸው የተባረከ እንዲሆን እንዲሁም ለሀገራችን ሰላም እና እድገት እንዲመጣ ይለምናሉ፡፡ በበጎ ልቦች ሕይዎቴ ጣፍጧልም ይላሉ፡፡

በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ነዋሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ሰንደቅ ጧሪ ቀባሪ ልጆችና ዘመድ የላቸውም፡፡ የጨጓራ እና ሌሎች ተጓዳኝ በሽታዎች ህመምተኛ የሆኑት በእድሜ የገፉት አረጋዊ ቤታቸው ጠባብ እና በክረምት ዝናብ የሚያስገባ ነበር፡፡ የዝናብ ፍሳሽ ወደ ቤታቸው ገብቶ ሁሉም የቤቱ ክፍል ጎርፍ ይሆንባቸው ነበር፡፡ የቤታቸም ግድግዳ የበሰበሰ፣ በር የሌለው፣ ጣሪያው ያረጀ እና የተቀደደ ነበር፡፡

ቢያገኙ በልተው ቢያጡ ጦም የሚያድሩት አቶ ተስፋዬ የቤታቸው ችግር ከህመማቸው ጋር ተጨምሮ ስቃያቸውን አባብሶት ነበር፡፡ ይህን ችግራቸውን የተረዱት የወረዳው በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በጉልበት፣ የአካባቢው ባለሃብቶች ደግሞ ገንዘብ በማዋጣት ቤታቸውን አፍርሰው እንደገና ሰርተውላቸዋል፡፡

ቤታቸው የታደሰላቸው አቶ ተስፋዬ ባልበላም አሁን በሞቀ ቤቴ ዝናብ ይዘንብብኛል ሳልል ያለስጋት ተኝቼ አድራለሁ ብለዋል፡፡ ይህን ላደረጉላቸው ለአካባቢው በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እና ባለሃብቶች እግዚአብሔር ወረታቸውን ይክፈላቸው ይላሉ አቶ ተስፋዬ፡፡

በጎ ፈቃደኛ ሀና ጉዲና በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በወረዳ 1 የበጎ ፈቃድ ስራ ትሰራለች፡፡ ከሶስት ዓመት ወዲህ የበጎ ፈቃድ ስራዋን የጀመረችው በጎ ፈቃደኛዋ አቅመ ደካሞችን በማገዝ፣ በማዕድ ማጋራት፣ የቤት እድሳት፣ ሃብት በማሰባሰብ ችግረኞችን እየረዳች ነው፡፡

የበጎ ፈቃድ ስራ ሰብዓዊነት እና ህሊና የሚረካበት ስራ ነው የምትለዋ በጎ ፈቃደኛ ሀና ሌሎች ወጣቶችም ወደ እነሱ ተግባር እንዲቀላቀሉ በማድረግ የተለያዩ የበጎ ፈቃድ ስራዎችን ይሰራሉ። ለችግረኞች ቤታቸውን በማፍረስ እንደገና ይሰሩላቸዋል፡፡ በጉልበታቸው ይረዳሉ፡፡

በፍሳሽ፣ በዝናብ እና በፀሐይ ሲሰቃዩ የነበሩት ወገኖች ቤታቸው ተሰርቶ ሲታይም የህሊና እርካታ እንደሚሰጥ ትገልጻለች፡፡ ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመሆን ለቀጣይም ይህን የበጎ ፈቃድ ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በጎ ፈቃደኛ ሀና ትናገራለች፡፡

ሁሉም ሰው በበጎ ፈቃድ ስራ ላይ እንዲሰማሩ የምትቀሰቅሰው ወጣቷ ያለምንም ቀስቃሽ ማህበራዊ ኃላፊነቱን የሚወጣ ወጣት እንዲጠናከር ትመክራለች፡፡

በልደታ ክፍለ ከተማ የበጎ ፈቃድ ስራ ከሚሰሩት እና ከሚያስተባብሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መካከል ወጣት ከመሸ ሀይለማሪያም አንዱ ነው፡፡ የበጎ ፈቃድ ስራውን ከጀመረ ረጅም ጊዜ የሆነው ወጣቱ የበጎ ፈቃድ ስራ እንደተቋም ከተደራጀ በኃላ በወረዳው እና ክፍለ ከተማው ላይ የበጎነት ስራውን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

የበጎ ፈቃድ ተሳትፎ ገደብ የሌለው መሆኑን ገልጾ ደም ልገሳ፣ ማዕድ ማጋራት፣ ቤት እድሳት፣ ጧሪ ረዳት ለሌላቸው እንደ አቶ ተስፋዬ አይነት አቅመ ደካሞችን ልብስና ገላ የማጠብ ስራዎችን እየሰሩ ነው፡፡

በጎ ፈቃደኛ ካሚል ጀማል የበጎ ፈቃደኛ ወጣት ከመሸን ሃሳብ  ይጋራል። በክፍለ ከተማው በሁሉም ወረዳዎች ላይ የበጎ ፈቃድ ስራ ላይ ተሳትፎ ያደርጋል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ እና ለበጎ ፈቃድ ስራ ለመቀስቀስና ለማስገንዘብ ያውላል፡፡ የተቸገሩ ሰዎችን እገዛ ያደርጋል፡፡ የበጎ ፈቃድ ስራ ውስጣዊ መሰጠትን ይጠይቃል የሚለው በጎ ፈቃደኛው ይህም ደመወዙ የህሊና እርካታ ነው ይላል፡፡

በደም ልገሳ፣ በመንገድ ትራፊክ ደህንነት ማስጠበቅ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ፣ አቅም የሌላቸው ሰዎች የነጻ ህክምና እንዲያገኙ ማገዝ፣ በጎነት በሆስፒታል እና በሌሎችም በጎ ተግባር ላይ ተሳትፎ ያደርጋል፡፡

የበጎ ፈቃድ ስራ ገደብ የለውም የሚለው ወጣቱ በበጎነት ተግባሩ እስከ ክልል ድረስ በመሄድ ድንበር የለሽ ተሳትፎ ያደርጋል፡፡ ሌሎች ወጣቶችም በበጎ ፈቃድ ተግባር ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ወጣት ካሚል ይጠይቃል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሶፎንያስ ፍስሐ በህብረተሰቡ ውስጥ ካሉ የተለያዩ ልማዶችና ወጎች ውስጥ እርስ በእርስ መረዳዳት አንዱ መገለጫ ነው ይላሉ፡፡

የበጎ ፈቃድ ስራው አቅመ ደካማ እና ምንም ጧሪ ድጋፍ የሌላቸው ወገኖች፣ ህመምተኞች፣ አካል ጉዳተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

የከተማዋ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የሚያደርጉት የበጎ ተግባር እጅግ የሚበረታታ ነው የሚሉት አቶ ሶፎንያስ ወጣቶቹ የበጎ ፈቃድ ስራን እና መረዳዳትን ባህል እንዲያደርጉት እና  ያለምንም ቀስቃሽ  ተሳትፎ እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጎ ፈቃደኛ የከተማዋ ባለሃብቶችም በበጎ ተግባር ስራ ላይ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የ2017 ዓ.ም የክረምት የበጎ ፈቃድ ተግባር በግንቦት ወር መጨረሻ እንደሚጀምር ገልጸው ፕሮግራሙም እስከ መስከረም 30 እንደሚቆይ ተናግረዋል፡፡

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በከተማዋ ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚደርሱ በጎ ፈቃደኞች በእያንዳንዱ ፕሮግራም በድግግሞሽ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

የበጎ ፈቃድ ተግባር ላይ በራሳቸው ፈቃድ በራሳቸው ተነሳሽነት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን የሚወጡ በጎ ፈቃደኞች በ15 መርሃ ግብሮች እና በ19 ንዑስ መርሃ ግብሮች ላይ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ አቶ ሶፎንያስ ተናግረዋል፡፡ የክረምት በጎ ፈቃድ የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን ገልጸው በቤት እድሳት፣ በማዕድ ማጋራት፣ በነጻ የህክምና አገልግሎት እና በመሳሰሉት መርሃ ግብሮች ከ900 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል፡፡

በየዓመቱ በበጎ ፈቃደኞች ብዙ ቢሊዮን ብር የሚገመት አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን አቶ ሶፎኒያስ ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና ባህሉም እየጎለበተ እና እያደገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review