በጎንደር የጥምቀት በዓል የሚከበርበት ስፍራ የእድሳት ስራ ተጠናቀቀ

You are currently viewing በጎንደር የጥምቀት በዓል የሚከበርበት ስፍራ የእድሳት ስራ ተጠናቀቀ

AMN-ጥር 7/2017 ዓ.ም

በጎንደር ከተማ የጥምቀት በዓል የሚከበርበት የፋሲለደስ መጠመቂያ ስፍራ የእድሳት ስራ ተጠናቆ ለበዓሉ ዝግጁ መደረጉን የከተማው ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ተወካይ ኃላፊ አቶ ልዕልና አበበ፣ የጥገና ስራ የተከናወነለት የፋሲለደስ መጠመቂያ ስፍራ ሁለት ሜትር ጥልቀት አለው፡፡

የጥምቀተ ባህሩን የውሃ ስርገት ለመከላከል የሚያስችል የጥገና ስራ መከናወኑን እና አሁን ላይም ከ10 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ ውሃ የመሙላት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በጥምቀተ ባህሩ መንበረ ታቦታቱ የሚያርፉባቸው ስፍራዎችን የማጽዳት እና ለምዕመናኑ ምቹ የማድረግ ስራዎች በአብዛኛው መጠናቀቃቸውንም ተናግረዋል፡፡

በበዓሉ የሚታደሙ የሀገር ውስጥና የውጪ ጎብኚዎችን ጨምሮ ለታላላቅ እንግዶች የሚውሉ የማረፊያ ስፍራዎች ደህንነታቸው በተጠበቀ መንገድ ዝግጁ መደረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡

እስከ 400 እንግዶችን ማስተናገድ የሚያስችሉ የብረት አግዳሚ ወንበሮች ጥራታቸውን በጠበቀ መንገድ ተሰርተው ለአገልግሎት መዘጋጀታቸውንም አመልክተዋል፡፡

ክብረ በዓሉን በቀጥታ ስርጭት ለሀገር ውስጥና ለመላው ዓለም ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ጊዜያዊ የቴሌቪዠን ማሰራጫ ስቱዲዮዎች የሚተከሉባቸው ስፍራዎች መደራጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

ጊዜያዊ መፀዳጃ ቤቶችን ጨምሮ የኤሌክትሪክ፣ የውሃ አና የኢንተርኔት አገልግሎቶችን የማሟላት ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀው፣ የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና መስጫ ቦታዎችም ተዘጋጅተዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review