በፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በሶማሊያ የስራ ጉብኝት አደረገ

You are currently viewing በፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በሶማሊያ የስራ ጉብኝት አደረገ

AMN-የካቲት 15/2017 ዓ.ም

በጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተመራ እና የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን ያካተተ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በሶማሊያ የአንድ ቀን የስራ ጉብኝት አድርጓል፡፡

ጉብኝቱ በቅርቡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሃሰን ሼክ ሙሀሙድ በአዲስ አበባ ባደረጉት ውይይት የቴክኒክ ውይይት በሞቃዲሾ እንዲደረግ መስማማታቸውን ተከትሎ የተካሄደ መሆኑ ተገልጿል።

የሶማሊያ ብሄራዊ ጦር ሀይሎች የመከላከያ ሰራዊት አዛዥ ሜጀር ጀነራል ኦዳዋ ዩሱፍ ራጌ እና የሶማሊያ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር አምባሳደር አብዱላሂ ሙሃመድ አሊ ልዑካን ቡድኑን ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሁለቱ አካላት ባደረጉት ውይይት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጠንካራ የሁለትዮሽ ትብብር ለማሳደግ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

በሶማሊያ እና አካባቢው ያለውን የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ በተደረገው ውይይት በአፍሪካ ቀንድና በአጠቃላይ በአፍሪካ አህጉር ሰላምና መረጋጋትን ማስጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እና ለቀጣናዊ ሰላም እያበረከተች ያለችውን አስተዋጽኦም አጠናክራ እንደምትቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የሚከተለው የሰከነ ዲፕሎማሲ እና ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጠው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲም ለአፍሪካ ቀንድ ብሎም ለአሕጉሪቱ ሰላም የላቀ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል፡፡

እኤአ ከ2007 ጀምሮ በሶማሊያ አልሸባብን ለመዋጋት በአሚሶም/አትሚስ እና ሌሎች የፀጥታ አካላት ለከፈሉት መስዋዕትነት ክብርና ምስጋና ተችሯቸዋል።

የአፍሪካ ህብረት በሶማሊያ ሰላም ለማስከበር የ (AUSSOM) ተልዕኮ መጀመሩን በደስታ መቀበላቸውን ገልጸዋል፡፡

ተልእኮው ቀድሞ በነበረው በአትሚስ የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑን አውስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት⁠ ሽብርተኝነትን በመዋጋት እና በቀጠናው ሰላም ለማስፈን የሚጫወተውን ሚናም አድንቀዋል።

ሁለቱ ሀገራት ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በጋራ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል፡፡

ዛሬ የተደረገው ውይይት የአንካራው ስምምነት ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ለመሆኑ ማሳያ እና ኢትዮጵያ ቅድሚያ ለጎረቤት የሚለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋን መርህ የሚያፀና መሆኑ ተመላክቷል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review