በፌደራል ተቋማትና ማህበራት ደረጃ የተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ውይይት ውጤታማ እንደነበር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ

You are currently viewing በፌደራል ተቋማትና ማህበራት ደረጃ የተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ውይይት ውጤታማ እንደነበር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ

AMN – ግንቦት 24/2017 ዓ.ም

በፌደራል ተቋማትና ማህበራት ደረጃ የተካሄደው 14ኛው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ህዝብን ወደ አንድነት የሚያመጡና ችግሮችን በግልጽ በመነጋገር በውጤት የተጠናቀቀ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ተናገሩ።

በቀጣይም የምክክር ሂደቱ ስኬታማና የምንፈልጋትን ሰላማዊት ሀገር ለማሻገር በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ወገኖች አሁንም አጀንዳዎቻቸውን ወደ ምክክር ቋቱ እንዲያስገቡ ጥሪ አቅርበዋል።

የሂደቱን መጠናቀቅ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጡት ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ኮሚሽኑ ለሶስት ቀናት ሲያካሄድ የቆየው የፌዴራልና ማህበራት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች የተነሱበት እንደነበር ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም በ11 ክልሎችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ማካሄዱን አስታወሰዋል።

በፌደራል ተቋማትና ማህበራት የተካሄደው የምክክር ምዕራፍ ከ38 በላይ ተቋማት መሳተፋቸውን ገልጸው፣ የተሰበሰቡ ሁሉም አጀንዳዎች ወደ ኮሚሽኑ ቋት መግባታቸውንም ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ እስካሁን ያካሄዳቸውን የምክክር ምዕራፍ በስኬት እያከናወነ መሆኑንም ፕሮፌሰር መስፍን ተናግረዋል።

ከሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰብ ጋር በተያያዘ ምክክሩ አካታች እንደመሆኑ የትግራይ ክልልን ተደራሽ ማድረግ በቀጣይ ኮሚሽኑ የሚያከናውነው ተግባር ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋርም አጀንዳ የማሰባሰብ መርሐ ግብር ይከናወናል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ወገኖች አጀንዳዎቻቸውን ወደ ምክክር ቋቱ እንዲያስገቡ ጥሪ አቅርበዋል።

አንዋር አህመድ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review