ባለፉት ሰባት አመታት በፌደራል ፖሊስ የተከናወኑ የለውጥ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለፁ።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ መጋቢት 24 ሀገራዊ ለውጥን ሰባተኛ አመት በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል።
በመርኃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤልን ጨምሮ፣ ምክትል ኮሚሽነሮች እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
ቀኑን አስመልክቶ “የመጋቢታውያን የለውጥ ፍሬዎች የነገ ተስፋዎች ትናንት፣ ዛሬና ነገን ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚሁ ጊዜ፥ ለውጡ ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የመነሳት ዘመን መሆኑን ጠቅሰው፥ በለውጡ በመታገዝ በፌዴራል ፖሊስ በርካታ ስኬታማ የሪፎርም ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል።
ተቋሙን በሰው ኃይል፣በቴክኖሎጂ ፣በአደረጃጀት፣በአሰራር፣የወደፊት እይታን ተረድቶ በመስራት ስኬታማ የሪፎርም ሥራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።
ለውጡ የፖሊስን የማድረግ አቅም በማሳደግ የወንጀል መከላከል እና የወንጀል ምርመራ ሥራዎችን ለማዘመን ማስቻሉን ተናግረዋል።
በዚህም ባለፉት ሰባት አመታት በተቋሙ የተከናወኑ የለውጥ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ፋንታ በበኩላቸው፥ ባለፉት አመታት የተከናወኑ የለውጥ ስራዎች ፌዴራል ፖሊስ በወንጀል መከላከልም ሆነ በወንጀል ምርመራ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ማስቻሉን ተናግረዋል።
ተቋሙ አሁን ላይ ተልዕኮውን በአግባቡ መፈጸም የሚያስችል ጠንካራ ኃይል መገንባት መቻሉን ነው የተናገሩት።
በመድረኩ የውይይት ፅሁፍ ያቀረቡት የተቋሙ የሰው ኃብት አስተዳደር ልማት ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ነብዩ ዳኘ፥ የለውጡ መንግስት የፀጥታና ደህንነት ተቋማትን በሙያዊ ብቃት፣ በተልዕኮ፣ በምላሽ አሰጣጥ እና በአደረጃጀት ማዘመን ላይ በትኩረት መስራቱን ተናግረዋል።