
AMN – ህዳር 4/2017 ዓ.ም
በፍራንኮ ቫሉታ ከውጭ የሚገቡ መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች በመደበኛ የንግድ ባንኮች የመተማመኛ ሰነድ /LC/ አማካኝነት እንዲገቡ መወሰኑን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ፡፡
መንግስት በመሰረታዊ የንግድ ሸቀጦች ላይ የምርት እጥረት እንዳይከሰት በማሰብ ለግል ባለሀብቶች ፍራንኮ ቫሉታ መፍቀዱ ይታወሳል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ እንዳሉት፤ ፍራንኮ ቫሉታ መሰረታዊ ሸቀጦችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት የምርት እጥረት እንዳይከሰት የተወሰነ እገዛ አድርጓል፡፡
ይሁን እንጂ የፍራንኮ ቫሉታ ባልተገባ መንገድ ለጥቁር ገበያ በመጋለጡ በውጭ ምንዛሬ ላይ ጫና በማሳደር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ አመዝኗል ብለዋል፡፡
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራው በመደበኛውና በትይዩ ገበያው መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሬ ተመን ተቀራራቢ በማድረጉ የፍራንኮ ቫሉታ እንዲነሳ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦችን በፍራንኮ ቫሉታ ወደ ሀገር ውስጥ የማስገባት ውሳኔ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም መደረጉንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በሂደት ላይ ያሉ ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦች በሁለት ሳምንታት ውስጥ እንዲገቡ እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡
በውሳኔው መሰረትም ከውጭ የሚመጡ መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች በንግድ ባንኮች የመተማመኛ ሰነድ ብቻ እንዲገቡ መወሰኑንና ይህም ወደ ተግባር መግባቱን ተናግረዋል።
የንግድ ባንኮች ለመረሰታዊ ሸቀጦች የሚሆን በቂ የውጭ ምንዛሬ ክምችት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ባንኮች ለሸቀጦች ትኩረት ሰጥተው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እንዲያሻሽሉ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡
መንግሥት የመሰረታዊ ሸቀጦችን አቅርቦትና ዋጋ በማረጋጋት የፖሊሲ ርምጃው ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
መንግስት በወሰዳቸው የቁጥጥርና የፖሊሲ ርምጃዎች በትይዩ ገበያውና በመደበኛ ገበያው መካከል ያለው ልዩነት በእጅጉ መጥበቡን አብራርተዋል፡፡
በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራው የውጭ ምንዛሬ ተመን መዋዠቅ አላጋጠመም ያሉት ሚኒስትሩ፤ በቀጣይም በብሄራዊ ባንክ በኩል የተጠናከረ ክትትል ይደረጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡