በኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የተመራ ከፍተኛ ልዑክ የአፍሪካና የአሜሪካ የቢዝነስ ጉባኤ ላይ ለመታደም በአንጎላ ርዕሰ መዲና ሉዋንዳ ገብቷል።
የዘንድሮውን የአፍሪካና የአሜሪካ የቢዝነስ ጉባኤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ አፍሪካን በተመለከተ የምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ድጋፍን መሰረት ካደረገው ወደ ንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለመቀየር መወሰኑን ተከትሎ የሚካሄድ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።
ዛሬን ጨምሮ ለአራት ቀናት በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የሁለቱም ወገን የቢዝነስ መሪዎችን ጨምሮ 1ሺህ 500 ተሳታፊዎች በጉባኤው ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ጉባኤው በአፍሪካና በአሜሪካ መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችና ዕድሎች ዙሪያ በመምከር ቀጣይ አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥ ታምኖበታል።
በጉባኤው ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ንግግር የሚያደርጉ ሲሆን ጎን ለጎንም የተለያዩ የሁለትዮሽ ውይይቶች እንደሚያደርጉ ኢዜአ ዘግቧል።