AMN-መጋቢት 7/2017 ዓ.ም
በፖለቲካው ዘርፍ የሴቶችን ተሳትፎ ለማጎልበት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የሴቶች ክንፍ “ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎን እናረጋግጥ” በሚል መርህ ውይይት አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የሴቶችን ተሳትፎና ተፎካካሪነት ለማረጋገጥ የሴቶች ክንፍ ከማቋቋም ጀምሮ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ያነሱት የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሙሉጌታ አበበ በዚህም ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ስለመቻሉ ተናግረዋል።
ሴቶች ባላቸው በሳልነት እና ውሳኔ ሰጭነት ሀገርን ባሻገሩ በርካታ ጉዳዮች ላይ የነበራቸው ሚናና አሁንም እያበረከቱት ያለው አስተዋፅኦ የጎላ መሆኑን ያነሱት ሰብሳቢው ይህንኑ አቅም በፖለቲካው ዘርፍም እንዲያጎለብቱ በማድረግ እና በፖለቲካዊ ፣በማህበራዊ፣ ኢኮሎሚያዊና በሰላም ፀጥታው ዘርፍም ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ምክር ቤቱ ከአቅም ግንባታ ጀምሮ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ስለመሆኑ አውስተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የሴቶች ክንፍ እንደ ሀገር እንብዛም የሆነውን የሴቶች ፖለቲካ ተሳትፎ በማጎልበት ረገድ ሚናው የጎላ ስለመሆኑም በመድረኩ ተመላክቷል።
በውይይት መድረኩም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና አልከድርን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ሰብሳቢና ሌሎች የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ተሳታፊ ሆነዋል።
በመድረኩ አፈ ጉባኤ ቡዜና አልከድር በፖለቲካው ዓለም ያካበቱዋቸውን የህይወት ዘመን የመሪነት ልምዳቸውን ለሴት ፖለቲከኞች አጋርተዋል።
በራሄል አበበ