በ2017 በጀት ዓመት በአገልግሎት ዘርፍ 7 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ይመዘገባል፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing በ2017 በጀት ዓመት በአገልግሎት ዘርፍ 7 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ይመዘገባል፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN – ጥቅምት 21/2017 ዓ.ም

በ2017 በጀት ዓመት በአገልግሎት ዘርፉ 7 ነጥብ 1 በመቶ እድገት እንደሚመዘገብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ እየተካሄደ ባለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ እና ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡

የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች በእጅጉ ለማሻሻል የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአብነትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ እየሰጠ ያለውን አገልገሎት ለማሻሻልና ለማዘመን የሚያስችሉ ራዎችን በመስራት በበጀት ዓመቱ 124 አውሮፕላኖች እንደሚገዙ ተናግረዋል፡፡

አየር መንገዱ አሁን ላይ በዓመት ከ20 እስከ 25 ሚሊየን የሚደርሱ መንገደኞችን የሚያስተናግድ ሲሆን በቀጣይ ከ100 እስከ 130 የሚደርሱ መንገደኞችን በዓመት ለማስተናገድ የሚያስችል ኤርፖርት ለማስገንባት ጥናት መጠናቀቁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

አዲስ የሚገነባው ኤርፖርት ከነባሩ ኤርፖርት 40 ኪሎ ሜትር የሚርቅ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሁለቱን ኤርፖርቶች በባቡር ትራንስፖርት በማገናኘት መጠቀም እንደሚቻልም አመላክተዋል፡፡

ይህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚሰጠው አገልግሎት ክብርና ዝናውን አስጠብቆ ከመሄዱ በተጨማሪ፣ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ውጤት እያስመዘገበ የሚቀጥል ተቋም ሆኖ እንደሚቀጥልም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስረዱት፡፡

እንደነዚህ አይነት ተቋማት በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ወደብ ለሌላቸው ሀገራት ወሳኝ መሆናቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒትሩ ይህም ለኢትዮጵያ ማንሰራራት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review