AMN – መጋቢት 3/2017 ዓ.ም
22ኛው የባህል ስፖርቶች ውድድር እና 18ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል ዛሬም ቀጥሎ የፈረስ ጉግስ እና ሸርጥ ውድድር ተካሂዷል።
አምስተኛ ቀኑን በያዘው 22ኛው የባህል ስፖርቶች ውድድር እና 18ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል ዛሬ ሹርቦ ዱባንቾ ሜዳ ላይ የፈረስ ጉግስ እና ሸርጥ ውድድር ተከናውኗል።
በሴቶች ፈረስ ሸርጥ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ኦሮሚያ፣ አማራ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ተሳትፈዋል።
በወንዶች ማዕከላዊ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሴቶች የተሳተፉ ሁሉም ክልሎች ተወዳድረዋል። በፈረስ ጉግስ ወንዶች አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጨምሮ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ተወዳድረዋል።
በፈረስ ሸርጥ ሴቶች ኦሮሚያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና አማራ ክልል ከአንድ እስከ ሦስት አጠናቀዋል።
በወንዶች የኦሮሚያ ክልል ተወዳዳሪ በቀዳሚነት ሲጨርስ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተወዳዳሪ ሁለተኛ፤ የደቡብ ምዕራብ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።
አስደናቂ ፉክክር በተደረገበት የፈረስ ጉግስ የወንዶች ውድድር የአዲስ አበባ ተወካይ በድል ሲጨርስ የአማራ ክልል ተወዳዳሪ ሁለተኛ ወጥቷል። ኦሮሚያ ደግሞ ሦስተኛ በመውጣት ውድድሩን አጠናቀዋል። አሸናፊዎቹም የተዘጋጀላቸውን የሜዳልያ ሽልማት ተቀብለዋል።
22ኛው የባህል ስፖርቶች ውድድር እና 18ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል እስከ መጋቢት ሰባት የሚቆይ ይሆናል።