
AMN-ግንቦት 02/2017 ዓ.ም
የዋንጫ ባለቤቱን እና ወራጆቹን የለየው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በአምስት ጨዋታዎች ይቀጥላል።
በቀጣይ የውድድር ዓመት የአውሮፓ ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ የሚደረገው ትንቅንቅ ሊጉን ለመከታተል ብቻ ተጠባቂ ምክንያት ይመስላል።
በወሳኝ ሰዓት የተሻለ ብቃት ማሳየት የጀመረው ማንችስተር ሲቲ ወደ ሴንት ሜሪ አቅንቶ ሳውዛምፕተንን ይገጥማል።
በ64 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ሲቲ ዛሬ ድል ከቀናው የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊነቱን አስተማማኝ ማድረግ ይችላል። ጨዋታው 11 ሰዓት ላይ ይጀምራል።
በተመሳሳይ ሰዓት ተጨማሪ ሦስት ጨዋታዎች ይከናወናሉ። ፉልሃም በሜዳው ክራቫን ኮቴጅ ኤቨርተንን ሲያስተናግድ መውረዱን ያረጋገጠው ኢፕስዊች ታውን ከ ብሬንትፎርድ ይጫወታል። ወልቭስ እና ብራይተን በሞሌንዩ የሚያደርጉትም ጨዋታ 11 ሰዓት ላይ ይጀምራል።
ምሽት 1:30 ላይ በቪታሊቲ ስታዲየም ቦርንማውዝ አስቶንቪላን ያስተናግዳል። በቀጣይ የውድድር ዓመት የአውሮፓ ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ ለሁቱም ክለቦች ትልቅ ትርጉም ያለው ጨዋታ ነው።
ዘንድሮ በቻምፒየንስ ሊጉ ሩብ ፍፃሜ መድረስ የቻለው ቪላ በ60 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ቦርንማውዝ በበኩሉ በ53 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በሸዋንግዛው ግርማ