ለንቅናቄው ስኬታማነት ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግ ተጠይቋል
አዲስ አበባ ልክ ከዘመናት እንቅልፍ እንደመንቃት፣ አሊያም የመቃብርን ድንጋይ ፈንቅሎ እንደመውጣት፣ በድቅድቅ ጨለማ እንደሌት ጨረቃ ፈክቶ እንደመታየት፣ ጉስቁልናውን አሽቀንጥሮ ጥሎ በአስደማሚ ጉልበት ታጅቦ እንደሚነሳ ንስር አሞራ የኋላ ቀርነትን ጨለማ ሰብራ እንደ ንጋት ኮከብ ደምቃ ትታያለች፡፡
በተለይም ሰውን ማዕከል ባደረጉት ፕሮጀክቶቿ የበርካቶችን እንባ እያበሰች፣ ደስታቸውን እየመለሰች ስለመሆኑ አያሌ ምስክሮችን ማንሳት እንችላለን። ወደ ትላንት ብዙም እርቀን ሳንሄድ በከተማዋ ማዕከላዊ ስፍራ የዶሮ ማነቂያን ያለፈ ጎስቋላ መልክ ከዛሬ ጋር አነፃፅረን ስንመለከት በርግጥም ከተማዋ በአቦ ሸማኔ ፍጥነት እራሷን ምን ያህል እያዘመነች እንደሆነ እንመለከታለን፡፡ ሁሉም ነገር የሚሰራው ለሰዎች ደስታ ነውና ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉ የመዲናዋ ነዋሪዎች ይህንን እውነት ይመሰክራሉ፡፡
˝ማን ይናገር የነበረ˝ እንዲሉ ባለትዳር እና የአራት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ሮማን ጌታቸው በዶሮ ማነቂያ አካባቢ ለ40 ዓመታት ኖረዋል፡፡ አኗኗራቸው ግን ሰው ለመኖር ከሚገባው በታች ነበር፡፡
በአንድ ግቢ ውስጥ ከ20 በላይ አባወራዎችና እማወራዎች ይኖሩ እንደነበር የሚያስታውሱት ወይዘሮ ሮማን እንደነገሩ በኮምፐርሳቶ እና በካርቶን የተከፈፈሉ ቤቶች፣ ላስቲክ እና የተቀዳደዱ ጨርቆችን ጣሪያና ግድግዳ ባደረጉ መጸዳጃ ቤቶች ዙሪያ 40 እና ከዚያ በላይ ሰዎች ሰልፍ የሚጠብቁበት፣ ሰው እንደዶሮ በቆጥ ውስጥ የሚኖርበት ያ! የዶሮ ማነቂያ ሕይወት የአዲስ አበባ የትላንት መልክ ማሳያ ነው፤ ይላሉ ወይዘሮ ሮማን፡፡ ዛሬ ወይዘሮ ሮማን በሰባ ደረጃ አካባቢ በተሰራው ምቹ የመኖሪያ ስፍራ ከቀድሞ ጎረቤቶቻቸው ጋር አዲስ ሕይወትን እየኮመኮሙ ነው፡፡
በመዲናዋ ሰውን ማዕከል ባደረጉ ልማቶች የከተማዋን ውበት እንደ አዲስ የገለጡ፤ የነዋሪውን ሕይወት ያጣፈጡ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ከሰሞኑ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማዋ ከሚኖሩ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት እና ከልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍል ከተውጣጡ ተወካዩች ጋር በከተማ እና ሀገር አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ በተደረጉ ተከታታይ ውይይቶች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ለአብነትም የከተማዋ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ “የወጣቶች ሚና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀው መድረክ ከአስራ አንዱም የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች ከተወጣጡ የወጣቶች ተወካዮች ጋር ተወያይተው ነበር፡፡
ወጣቶቹ ከከንቲባዋ ጋር ባደረጉት ውይይትም ከለውጡ ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው አጀንዳዎች መካከል ወጣቶች በአካል እና በስነ ልቦና ተገንብተዉ አስተማማኝ የስራ ዕድል እንዲያገኙ ለማስቻል በተሰራው ስራ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን እና በውጤቱም ተጠቃሚ መሆናቸውን መስክረዋል፡፡
ውይይቱን አስመልክቶ ከንቲባዋ ባስተላለፉት መልዕክትም ከ1400 በላይ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች መገንባታቸውን እና ባለፉት 5 ዓመታት ብቻ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ወጣቶች ቋሚ የስራ ዕድሎችን እንዲያገኙ ለማስቻል በተከናወነው ስራ የበርካታዎችን ሕይወት በተጨባጭ መለወጥ መቻሉን አረጋግጠውልናል፤ ብለዋል።

በሌላ በኩልም “ብቃት ያለው ሲቪል ሰርቪስ ለኢትዮጵያ ብልጽግና “ በሚል መሪ ሀሳብ ከወረዳ እስከ ከተማ ማዕከል ካሉ ተቋማት ከተውጣጡ የመንግሥት ሰራተኞች ተወካዮች ጋር በከተማዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ተደርጓል። በዚሁ ወቅት ከንቲባዋ ባስተላለፉት መልዕክት አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለጎብኚዎቿ አስተማማኝ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን በየደረጃው ካለው የመንግሥት ሰራተኛ ጋር በጋራ በመሆን ከከተማዋ ገቢ 71 በመቶውን ለዘላቂ ልማት ስራዎች በማዋል ውጤቶችን ማስመዝገብ ችለናል ብለዋል።
ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በከተማ ደረጃ ሁሉንም ክፍለ ከተማዎች ወክለው ከመጡ የአዲስ አበባ ሴቶች ጋር “የሴቶች ሚና ለሁለንተናዊ ብልፅግና “ በሚል መርህ በከተማ አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያም ውይይት አድርገዋል፡፡ በዚሁ ወቅት በአዲስ አበባ የሴቶችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን አቅዶ በመስራት ዉጤቶች ስለመመዝገባቸውም ጠቅሰዋል፡፡
ለአብነትም በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች፣ በንግድና አገልግሎት ዘርፎች መሰማራት እንዲችሉ፤ ጀማሪዎችም በእንጀራና ዳቦ ፋብሪካዎች፣ በአነስተኛና ጥቃቅን፣ በአረንጓዴ ልማትና ከተማ ዉበት፣ በመጋቢ እናትነት፣ በሴፍቲኔት ፕሮግራም ከተረጂነት ወደ አምራችነት እንዲሸጋገሩ በማስቻል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች የስራ እድልና ገቢ እንዲያገኙ እድል ተፈጥሮላቸዉ ኑሯቸዉን እያሻሻሉ ለሌሎችም የስራ እድል በመፍጠር ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በየጎዳናዉ ለብዙ ማህበራዊ ስብራት ተጋልጠው የነበሩ እህቶች “ለነገዋ” የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ውስጥ በመገንባት የስነ ልቦና ህክምና እና የሞያ ስልጠና ወስደው ተጨባጭ እና ምሳሌ በሚሆኑ ስራዎች ላይ ስለመሰማራታቸውም ለአብነት አንስተዋል፡፡
እንደከተማ ከተደረጉት ህዝባዊ ውይይቶች መካከል “ሀገር እና ጥበብ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው መድረክ አንዱ ነው። መድረኩ ኪነ ጥበብ የሀገርና የትውልድ ግንባታ አምባ መሆኑን በመገንዘብ በከተማዋ የሚከናወኑ የለውጥ ስራዎች የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ተሳትፎ ያረጋግጥ ዘንድ በትብብር ለመስራት የተዘጋጀ ነዉ። ይህንን መሰል ውይይቶች በከተማዋ እየተከናወኑ ሲሆን እንደከተማ የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠልም ውይይቶቹ ትልቅ አበርክቶ እንዳላቸው የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያና የስነ ልቦና አማካሪ አቶ መሀደር ሳልህ ይናገራሉ፡፡
የማህራዊ ሳይንስ ባለሙያው እንደሚሉት ማንኛውም ልማት የሚሰራው ለሕዝቦች ኑሮ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር በመሆኑ ስራዎችን ከህዝብ ጋር እየተወያዩ መስራት የማህበረሰቡን ችግር በዘላቂነት ቀርፎ ዕድገትንና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ያለው ድርሻ ከፍ ያለ ነው፡፡ ህዝቦችን እያወያዩ መስራት ተጨባጭ ልማትን እንደሚያመጣም ተናግረዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ጋር ሰፋ ያለ ውይይቶችን ካደረጉ በኋላ ባሳለፍነው ሐሙስ ለቀጣይ 90 ቀናት በሚከናወነው ልዩ የንቅናቄ አጀንዳ ዙሪያ ለመላው አመራር የስራ አቅጣጫን ሰጥተዋል።
ይህ የልዩ ተልዕኮ አጀንዳ ከሰኔ 5 እስከ ጳጉሜ 5 ባሉ 90 ቀናት የሚከናወን ነው፡፡ ንቅናቄው 18 ዋና ዋና ተግባራትን አካትቶ ይዟል። ከእነዚህ የንቅናቄ አጀንዳዎች መካከል የከተማ ግብርናን ማስፋፋት፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ማሳካት፣ የክረምት በጎ ፍቃድ ስራዎች፣ የኑሮ ውድነትን መቆጣጠር፣ ሁለተኛ ዙር ኮሪደር ልማትን ማጠናቀቅ፣ የትምህርት ለትውልድ ኢኒሼቲቭ፣ ገቢን ማሳደግ፣ እየተገነቡ የሚገኙ ትላልቅ ፕሮጄክቶችን (Mega Projects) አጠናቅቆ ለህዝብ ክፍት ማድረግ፣ ስራ ዕድል ፈጠራ እና ፍትሐዊ አገልግሎትን ለህዝባችን ተደራሽ ማድረግ አንኳሮቹ ናቸው።

እነዚህንና ተያያዥ የለውጥ የንቅናቄ ተግባራትን ለማሳካት አመራሩ በተቀናጀና በተናበበ መልኩ በመንቀሳቀስ የህዝባችን ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይገባዋል ያሉት ከንቲባዋ የዚህ ልዩ ተልዕኮ ዋነኛው ፈጻሚ ሀይል ደግሞ ከማዕከል ጀምሮ እስከ ወረዳ ያሉ ተቋሞችና የአስተዳደር አካላት ይሆናሉ ብለዋል።
በመሆኑም ሁሉም ተቋማት ምን ያህል “ሰራተኛን የልማት አቅም ማድረግ ችለናል?” የሚለዉ ዋነኛ መመዘኛችን ይሆናል ያሉት ከንቲባ አዳነች ትልቁ የልማታችን ሞተር የሆነው የህዝባችንን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥብቅ የድጋፍና ክትትል ስርዓት በመዘርጋት እያንዳንዱን የንቅናቄ አጀንዳ ስኬታማነት ኦዲት እያደረግን እንሄዳለን ብለዋል።
እንደ ማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው አቶ ማህደር ሳልህ ገለፃ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ እንደ ከተማም ሆነ እንደ ሀገር በዘጠና ቀናት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ቀደም ባሉት ዘመናት ብዙ ዓመታትን ይወስዶ የነበሩ ፕሮጀክቶችን የሚያክሉ ናቸው፡፡ በተለይም ሰውን መሰረት ያደረጉ ልማቶች በመሆናቸው ባለፉት ጥቂት ዓመታት የበርካታ ድሃዎችን እንባ ያበሱ ፈገግታቸውንም የመለሱ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡
ለአብነትም የተጎሳቆሉ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ባማረ ሁኔታ ወደተገነቡ ቤቶችና መንደሮች ማዘዋወር፣ ባሉበት ቦታም ቤታቸውን በዘመናዊ መልክ ማደስ፣ የልጆች መጫዎቻ ስፍራዎችን እና የወጣቶች ስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች እና መሰል የመናፈሻ ስፍራዎች ተገንብተው ለአገልግሎት ሲበቁ ተመልክተናል ብለዋል፡፡
ከሰሞኑም ከተማ አስተዳደሩ ለቀጣይ 90 ቀናት በሚከናወነው ልዩ የንቅናቄ አጀንዳን ይፋ ማድረጉን የጠቀሱት የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው አጀንዳዎቹ ቀደም ባሉት ዓመታት እየተከናወኑ እንደ ከተማ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገርም በተምሳሌትነት የሚጠቀሱ ውጤቶችን ያስመዘገቡ እንደሆኑም ገልፀዋል፡፡

ቀደም ሲል በተከናወኑ የከተማ ግብርና ስራዎች ሰው ባለችው ትንሽ ቦታም ቢሆን እራሱን ከመደጎም አልፎ ለሌሎችም መትረፍ የቻለበት ነው፡፡ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም ከተማዋን አረንጓዴ በማልበስ ከተፈጥሮ ጋር ማስታረቅ የተቻለበት ውጤት እየተመዘገበ ነው፡፡ በክረምት በጎ ፍቃድ ስራዎችም የአቅመ ደካሞችን ቤት ከማደስ እስከ ደም መለገስ በደረሱ በጎ ስራዎች ትውልዱን ማሳተፍ የተቻለበት ተግባር ተከናውኗል። በኮሪደር ልማቱም ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና ተመራጭ ማድረግ ተችሏል፡፡
በሌላ በኩልም በኑሮ ውድነት፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በትምህርት ለትውልድ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ማህበረሰቡን ያሳተፉና ተጠቃሚም ያደረገ ውጤት የተመዘገቡባቸው ተግባራት በመሆናቸው ከተማ አስተዳደሩ እነዚህን ለውጥ ማምጣት የቻለባቸውን ተግባራት የዘጠና ቀናት የልዩ ተልዕኮ አጀንዳ አድርጎ ለተግባራዊነቱ መነሳቱ ህዝብን ማዕከል አድርጎ ለሚሰራቸው ተግባራት ዋስትና በመሆናቸው ከአመራሩና ከባለሙያው ባሻገር ሁሉም የመዲናዋ ነዋሪ ለስኬታማነታቸው ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባም የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
በመለሰ ተሰጋ