ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከደረሱት ሰብሎች 53 ሚሊየን ኩንታል ምርት መሰብሰቡ ተገለጸ

AMN ህዳር 19/2017 ዓ.ም

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከደረሱት ሰብሎች 53 ሚሊየን ኩንታል ምርት ተሰብስቦ ወደ ጎተራ መግባቱን የግብርና ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ኢሳያስ ለማ፤ በዘንድሮ የመኸር ወቅት 607 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል፡፡

የታቀደውን ግብ ለማሳካትም የድህረ ምርት ብክነትን መቀነስ የሚያስችሉ የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎችን በመተግበር የደረሱ ሰብሎችን በጥንቃቄ ሰብስቦ ወደ ጎተራ ማስገባት ይገባል ብለዋል፡፡

እህሉን በወቅቱ ከማሳ አለመሰብሰብ፣ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂን አለመጠቀም፣ በወቅቱ ወቅቶ ወደ ጐተራ አለማስገባትና እህሉ ተገቢውን የእርጥበት ደረጃ ላይ ሳይደርስ ወደ ጎተራ ማስገባት የድህረ-ምርት ብክነትን የሚያስከትሉ ተግባራት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም የጎተራ ተባዮችን ሊቀንስ የሚችል የእህል ማከማቻ አለመጠቀም፣ የከረመና አዲስ እህልን ቀላቅሎ ማስቀመጥ፣ የጎተራና እህል ማከማቻዎችን በአግባቡ ያለማፅዳት እና ፀረ- ተባይ መድሃኒቶችን በአግባቡ አለመጠቀም በዋነኛነት የድህረ-ምርት ብክነትን እንደሚያስከትሉ ጠቅሰዋል፡፡

በብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ትንበያ መሰረት በሚቀጥሉት ቀናት ከሚኖረው የአየር እርጥበት ጋር ተያይዞ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊዘንብ እንደሚችል አቶ ኢሳያስ ጠቁመዋል፡፡

ስለሆነም የደረሱ ሰብሎችን በጊዜ በመሰብሰብ በጥንቃቄ ወደ ጎተራ ማስገባት እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review