AMN- ጥር 12/2017 ዓ.ም
ባለፉት ስድስት ወራት በወጪ ንግድ ዘርፍ 3 ነጥብ 28 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለፁ።
“በጥራት ወደ ተሳለጠ የንግድ ስርዓት” በሚል መሪ ቃል የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው።
መድረኩን አስመልክተው ሚኒስትሩ በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት፣ ባለፉት ስድስት ወራት በወጪ ንግድ ዘርፍ 3 ነጥብ 28 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡
በሌላ በኩል የጥራት መንደር ኢትዮጵያን በሚወክልና በሚያስደንቅ ደረጃ መጠናቀቁ ለሃገር ኩራት ማዕከል ሆኖ የተሳካ ስራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
በኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፍቃድ አሰጣጥ ለንግድ ስርዓት ምቹ እንዲሆን ውጤታማ ስራ ተሰርቷል ያሉት ሚኒስትሩ በዚህ ረገድ ብልሹ አሰራሮችን ከማረም አንጻር ህገ ወጥ ተግባር በፈጸሙ 18 የተቋሙ ሰራተኞች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስድስት ወራት ከ2 ሚሊዮን 50 ሺህ በላይ የንግድና ምዘገባ ፍቃድ አገልግሎት መሰጠቱን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ይህ ውጤት ያለፈው በጀት ዓመት ከተከናወነው 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዓመታዊ አፈጻጸም አንፃር ሲታይ በጣም ከፍተኛ አፈፃፀም መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ነዳጅ ግብይትን ሰርዓት ለማስያዝ በተሰራ ስራ በህገ-ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 325 ሺ ሊትር ነዳጅ በቁጥጥር ስር መዋሉን ነው ሚኒስትሩ የገለፁት።ኩባንያዎች 116 ሚሊዮን ብር እንዲቀጡ ተደርጓልም ብለዋል፡፡

የሲሚንቶ ግብይት ላይ በተወሰደ የአሰራር ሰርዓት ማሻሻያ የተረጋጋ አቅርቦትና ግብይት እንዲኖር በመደረጉ ዋጋው በግማሽ መቀነሱን አስታውቀዋል፡፡
በተመሳሳይ መንገድ የጨው ግበይት ሪፎርም በማድረግ በጥቂት ነጋዴዎች በሞኖፖልሊ ተይዞ የነበረውን ግብይት በፍትሃዊነት ለሁሉም ክፍት እንዲሆን መደረጉን ጠቁመዋል።
የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ተቋርጦ ከነበረበት ምዕራፍ በማውጣት ወደ ንቁ ድርድር አውድ የገባ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ ለቀጣይ 5ኛ ዙር ድርድርም ብቃት ያላቸውን ሙያተኞችን በማደራጀት በቂ ዝግጅት በመደረግ ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል።