AMN-ጥር 15/2017 ዓ.ም
ባለፉት ስድስት ወራት መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ሃብት መሰብሰቡን የአዲስ አበባ ማህበራዊ ትረስት ፈንድ አስታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማህበራዊ ትረስት ፈንድ ጽ/ቤት የ2017 በጀት ዓመት የ6 ወር የስራ አፈጻጸም ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።
የማህበራዊ ትረስት ፈንድ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አስራት ንጉሴ፣ ጽህፈት ቤቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ለማህበራዊ ቀውስ የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከለጋሾች፣ ከባለሃብቶች ከመንግስት የልማት ድርጅቶች፣ ከንግዱ ማህበረሰቦች ከሃይማኖት ተቋማትና ከበጎ ፈቃደኞች ሃብት በመሠብሰብ ተጠቃሚዎችን በመለየት በአግባቡ በማስተላለፍ ለታለመለት ድጋፍ በትክክል መዋሉን እንደሚከታተል ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ ባለድርሻ አካላት አጋርነት ባለፉት 6 ወራት አበረታች ስራዎች ስለመሰራታቸውም ጠቅሰዋል።
መስጠት መታደል ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ የተቸገሩ ወገኖችን ለማቋቋም ሲተርፈን ብቻ ሳይሆን ካለን ቀንሰን በመስጠት ለወገን አለኝታነታችንን ልናረጋግጥ ይገባናል ነው ያሉት።
የሃብት ማሰባሰብ ሂደቱ ከሰው ንክኪ በጸዳ መልኩ ከባንኮችና ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመቀናጀት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚከናወን ስለመሆኑም ነው ወ/ሮ አስራት የተናገሩት።
በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 6 ወር ከተለያዩ አካላት ሃብት በማሰባሰብ ትረስት ፈንዱ ጠንካራ ስራ ሲሰራ የቆየ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለጽህፈት ቤቱ 9 ሚሊዮን ብር በመለገስ በትልቁ ማህበራዊ ኃላፊነቱን የተወጣ ተቋም መሆኑ በቀረበው ሪፖርት ተመላክቷል።
ሌሎች ከተቋሙ ጋር በአጋርነት እየሠሩ ያሉ በርካታ ተቋማት ያሉ መሆኑን በማንሳት የአፍሪካ ህብረት፣ ታፍ ኦይል ኩባንያ፣ አፍሪካ ሆልዲንግ ግሩፕ እና የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዋናዎቹ ስለመሆናቸው ተብራርቷል።
ባለፉት 6 ወራት ከመንግስታዊ ተቋማት 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ሃብት የተሰበሰበ ሲሆን መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ደግሞ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል።
በአጠቃላይ በግማሽ አመቱ 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር እንደተሰበሰበ በቀረበው ሪፖርት ተመላክቷል።
በምትኩ ተሾመ