
AMN – ግንቦት 7/2017 ዓ.ም
መንግስት የኮንፍረንስ ቱሪዝምን ለማስፋፋት በሰራው ስራ ባለፉት አስር ወራት ብቻ 84 ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች በተለያዩ ተቋማት አስተናጋጅነት በኢትዮጵያ መደረጋቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡
ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባትም ባለፉት ዓመታት ዘርፉን ለማሳደግ ሰፊ ስራ መሰራቱን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ዘርፉ እንደ አንድ የኢኮኖሚ ሴክተር ትኩረት ተሰጥቶት ወደ ስራ ሲገባ በዋነኝነት ሁለት ጉዳዮችን በመስራት መሆኑንም የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ገልፀዋል፡፡
እነዚህ በአዲስ አበባ እና በመላ ሀገሪቱ የተገነቡ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በመጠቀም ባለፉት 10 ወራት 84 ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በተለያዩ ተቋማት አስተናጋጅነት በኢትዮጵያ ማድረግ መቻሉንም ሚኒስትር ዴኤታው በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡
ከቱሪዝም ዘርፍ በተጨማሪ ከአምራች ኢንዱስትሪው የሚገኘውን ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተሰሩት ስራዎች ውጤት ማምጣቸውን የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ መጠን ያለውን ከውጭ የሚገባ ምርት ማስቀረት ተችሏል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለአምራቾች በተደረጉ የተለያዩ ድጋፎች ምክንያት የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አማካይ አቅም ከፍ ማድረግ ተችሏል ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡
በአሰግድ ኪ/ማርያም