
AMN-ህዳር 2/2017 ዓ.ም
ባለፉት 5 ዓመታት ብልፅግና ፓርቲ ፈተናዎችን በመቋቋም አንጸባራቂ ድሎችን ማስመዝገብ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ገለጹ፡፡
ኃላፊው ይህንን ያሉት የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በ2017 ሩብ ዓመት በፖለቲካ፤ በአደረጃጀት እንዲሁም በአቅም ግንባታ ዘርፍ የተከናወኑ ስራዎችን በገመገመበት መድረክ ላይ ነው፡፡
በ5 ዓመታት የተገኙ ስኬቶችንና ያጋጠሙ ችግሮችን መለየት የሚያስችሉ የተለያዩ መድረኮች በመካሄድ ላይ ናቸው ያሉት ኃላፊው ተመሳሳይ መድረኮች እስከ ህዳር ወር መጨረሻ ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
ባለፉት 3 ወራት ሰፋፊ የአቅም ግንባታና የንቅናቄ ስራዎች መሰራታቸውን የጠቀሱት አቶ ሞገስ ተቋማዊ ግንባታን ከማረጋገጥ ባለፈ ፓርቲው ተጽዕኖዎችን መቋቋም የሚችል ጠንካራ ፓርቲ እንዲሆን አመራሩ ሃላፊነት አለበት ብለዋል፡፡
ፓርቲው የሩብ ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እንዲሁም የ5ኛ ዓመት የፓርቲ ምስረታ በዓሉን ባከበረበት መድረክ ላይ ከማዕከል እስከ ወረዳ ያሉ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
በትዕግስት መንግስቱ