AMN – የካቲት 11/2017 ዓ.ም
ባለፉት 6 ወራት በአዲስ አበባ የወንጀል ምጣኔ ከቀደሙት ጊዜያት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ42 በመቶ መቀነሱን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታውቋል፡፡
ቢሮው በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 6 ወራት ህብረተሰቡን ያሳተፈ የሰላም ግንባታ እና ወንጀልን የመከላከል ስራ የሽብርና የጽንፍ ሃይሎች እንቅስቃሴ በመቀልበስ የህግ የበላይነት ማረጋገጥ መቻሉን ለኤ ኤም ኤን በላከው ያለፉት 6 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
የጸጥታ ስራዎችና አገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ማከናወን የሚያስችል የቴክኖሎጂ ልማት ማካሄድ መቻሉን ያወሳው ቢሮው በዚህም የኢኮኖሚ አሻጥርና ሌሎች ህገ ወጥ ተግባራት በመከላከልና በመቆጣጠር የተረጋጋ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲኖር ማድረግ ተችሏል ብሏል፡፡
በግማሽ አመቱ 558 ከባድ ወንጀሎች መፈጸማቸውን የጠቆመው ቢሮው ይህም ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ሲነጻጸር በ42 በመቶ መቀነሱን አብራርቷል፡፡
ህዝባዊና ኃይማኖታዊ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ከተማ አቀፍ ንቅናቄ በመፍጠር ከህዝቡ፣ ከሃይማኖት ተቋማት ፣ ከአደረጃጀቶች እና ከፀጥታ ተቋማት ጋር በቅንጅትና በትብብር መስራት በመቻሉ በዓላቱ ካለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲከበሩ መደረጉን አስታውቋል፡፡
ቢሮው ህብረተሰቡን የሰላም ባለቤት ማድረጉ በየደረጃው የህዝብ ተሳትፎ ስራዎች እና የተለያዩ የህዝብ አደረጃጀቶች ማጠናከሩ እንዲሁም በሰላምና በጸጥታ ስራዎች ላይ ማሳተፍ መቻሉ ለመዲናዋ ሰላም እና ጸጥታ መስፈንና መረጋገጥ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጿል፡፡
ከትምህርት ተቋማት ውጭ ለጸጥታ ስጋት የሆኑ አዋኪ ድርጊቶችን የመቆጣጠር’ የመከታተል እና የእርምት እርምጃ መወሰዱን ያስታወቀው ቢሮው 21 ሺህ 546 የጎዳና ተዳዳሪዎችን በማንሳት ማቆያ እንዲገቡና ከእነዚህ ውስጥ ለ1ሺህ 150 የስራ ዕድል መፍጠሩን አመልክቷል፡፡
16 ሺህ 413 የሚሆኑት ደግሞ ወደ ክልል እንዲሸኙ መደረጉን ገልጿል፡፡
በባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ከ 8 ክፍለ ከተሞች የተለዩ 2ሺህ 729 ባጃጆች ህጋዊ መስፈርቱን በማሟላታቸው አገልግሎት እንዲጀምሩ መደረጉን ቢሮው ጠቁሟል።
1ሺህ 534 የሚሆኑ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እና የገንዘብ ዝውውር ፣ ሀሰተኛ የገንዘብ ህትመት እና ሌሎች ቀላልና ከባድ ወንጀሎችን የመከላከል እና እርምጃ የመውሰድ ስራ መከናወኑንም ቢሮው አስታውቋል፡፡
የኑሮ ውድነትን የሚያባብስ ህገ ወጥ ንግድ ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልጿል፡፡
1 ሚሊየን 440 ሺህ 947 ለሚሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሰላምና ፀጥታ እንዱሁም በሀገራዊ ጉዳዩች ዙሪያ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ቢሮው ጠቅሷል፡፡
ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ 142 ሺህ 733 ተሳታፊዎች የታደሙበት የሠላም ኮንፍረንሶች እንዲሁም የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ እና 2 ሚሊየን 497 ሺህ 934 ተሳታፊዎች የተገኙበት ማህበረሰብ ተኮር ውይይቶች መካሄዳቸውን ቢሮው ገልጿል፡፡
3 ሚሊየን 756 ሺህ 297 የሚሆኑ የሰላም ሰራዊት አባላት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ከጸጥታ አካላት ጋር ቅንጅት በመፍጠር አካባቢያቸውን በመጠበቅ የተለያዩ ወንጀሎች እንዲከላከሉ መደረጉንም ቢሮው አመልክቷል፡፡
በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት 21 ሺህ 23 አዲስ የሰላም ሰራዊት አባላት የመመልመል፤ የማጠናከር፤ የማደራጀት እና ወደ ስምሪት የማስገባት ስራዎች መከናወናቸውንም ጠቅሷል፡፡
ሰነድ ከማጭበርበርና ሀሰተኛ ህትመትን ከመከላከል እንዲሁም ከመሬት ወረራና ከቡድን ጸብ ጋር ተያይዘው ሊከሰቱ የሚችሉ ስጋቶች ላይ ቀድሞ እርምጃ መወሰዱን ያመለከተው ቢሮው በ566 የጸረ-ሰላም ሃይሎች እኩይ ተግባር ላይ እርምጃ መወሰዱን አመላክቷል፡፡
በትምህርት ቤቶች ዙሪያ በሚገኙ ህገወጥ ማሳጅ ቤት፣ ፔንሲዮን፣ ገስት ሀውስ፣ አረቄ ቤት ቁማር ቤት በመሳሰሉት ላይ ከፀጥታ አካል ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ እርምጃ መወሰዱንም ቢሮው በሪፖርቱ አብራርቷል፡፡
በሰለሞን በቀለ