ባሕር ዳር ተፈጥሮ እና የሰው ጥበብ ሲሠናኙ ምን ሊፈጥሩ እንደሚችሉ እያሳየች ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች በባህርዳር የልማት ሥራዎችን እየጎበኙ ነው።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ ሚኒስትሮች እና ሌሎችም ከፍተኛ አመራሮች ባሕር ዳር ከተማ ገብተዋል።
ከፍተኛ አመራሮቹ ባሕር ዳር ከተማ ሲደርሱ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የባሕር ዳር ከተማ የሥራ ኀላፊዎች፣የሃይማኖት አባቶች፣የሀገር ሽማግሌዎች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮቹ ከአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በከተማዋ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው እየጎበኙ ናቸው።
በጣና ሐይቅ ላይ የሚገነባውን ጣና ማሪና ሪዞርት፣አዲሱን የዓባይ ድልድይ፣ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም፣ የኮሪደር ልማት እና ሌሎችንም የልማት ሥራዎች ነው እየተመለከቱ የሚገኙት።
በዚሁ ወቅትም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የአማራ ክልል የሥራ ኃላፊዎች እና የባሕር ዳር ከተማ ሕዝብ ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ላደረጋችሁት ደማቅ አቀባበል ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል፡፡
ባሕር ዳር ተፈጥሮ እና የሰው ጥበብ ሲሠናኙ ምን ሊፈጥሩ እንደሚችሉ እያሳየች ነው ሲሉም ገልጸዋል።