AMN – ጥር 22/2017 ዓ.ም
ብልጽግና ፓርቲ ቃሉን በተግባር ለመፈጸሙ አንዱ እና ትልቁ ማሳያ አዲስ አበባ ከተማ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
“ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ቃል ነገና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ የሚደረገውን የብልፅግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ የመጡ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን እየጎበኙ ነው፡
ጉብኝቱን አስመልክተው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለ ኤ ኤም ኤን በሰጡት ማብራሪያ፣ ብልጽግና ፓርቲ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ አበባ እናደርጋታለን የሚል ቃል ገብቶ እንደነበር እና ጉብኝቱም ይህ ቃል በተግባር መፈጸሙን ለመመልከት የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያን ብዝሃነት የሚያሳይ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የተወከሉበት ፓርቲ መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ “ብዝሃነታችንን ጠብቀን ጠንካራ ሀገር ለመገንባት እየሰራን ነው” ብለዋል፡፡
በእያንዳንዱ አካባቢ የሚገነባው ስራ ከአካባቢ ልማት ባለፈ ሀገር የመገንባት ስራ መሆኑን ነው ከንቲባዋ ያወሱት፡፡
ያለፉት ሶስት ዓመታት አዲስ አበባ የገባችውን ቃል በተግባር የፈጸመችበት ዓመታት ናቸው ያሉት ከንቲባዋ የፓርቲው አመራሮችና አባላትም ባደረጉት ጉብኝት ይህንኑ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የሰራቸው የልማት ስራዎች ከህዝብ ጋር የነበረን መተማመን ማጠናከሩንም ጠቁመዋል፡፡
የሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ስራ ነዋሪዎችን ያሳተፈ እንዲሁም ህብረተሰቡንም ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑን ነው ከንቲባዋ የገለጹት፡፡
በመዲናዋ እየተሰራ ያለው ዘርፈ ብዙ የልማት ስራ ከከተማዋ የመልማት ፍላጎት አንጻር በቂ ባለመሆኑ ወደፊት ስራውን ባህል አድርጎ ለመሄድ መታቀዱንም ተናግረዋል፡፡
እየተሰራ ያለው ስራ አዲስ አበባን በቱሪስት መዳረሻነት ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃ እንድትይዝ ማስቻሉንም ከንቲባዋ አስታውሰዋል፡፡
በሰፊና ሁሴን