AMN-ጥር 18 ቀን 2017 ዓ.ም
ብልፅግና ፓርቲ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ውሳኔ እንድንሰጥ ዕድል ፈጥሯል ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።
ከለውጡ በኋላ በክልሉ የተገኙ ስኬቶችን በተመለከተ መግለጫ የሰጡት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ብልፅግና ፓርቲ የመደመር እሳቤን ተግባራዊ በማድረግ ከዚህ በፊት የውሳኔ አካል ያልነበሩ ክልሎች ውሳኔ ሰጪ እንዲሆኑ አድርጓል ብለዋል።
ፓርቲው ከለውጡ በፊት በፖለቲካው መስክ ተገልለው የቆዩ ክልሎች ድምፃቸው እንዲሰማ ማድረጉንም አስታውሰዋል።
የክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት ስራ አስፈጻሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው በማንኛውም ሀገራዊ አጀንዳ ላይ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ፖለቲካዊ ስኬት ነው ብለዋል።
ለውጡ ለክልሉ ህዝብ ያስገኘው የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም የተፈጥሮ ሀብት በአካባቢው ህብረተሰብ እንዲለማና ተጠቃሚ እንዲሆን የተቀረፁ ፖሊሲዎች ውጤታማ መሆናቸውን አክለዋል።
በማዕድን፣ በግብርና እና ሌሎች ዘርፎች በርካታ የክልሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ኑሮውን እየመራ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።
ክልሉ አጋጥሞት የነበረውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት ባደረገው ጥረት ታጣቂ ኃይሎች የሰላምን መንገድ እንዲመርጡ መደረጉን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
የሰላም ተመላሾችም በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው የለውጡ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ጠቅሰዋል።
ለአብነትም በ2016 በጀት ዓመት 300 ሚሊየን ብር በመመደብ ትራክተር፣ ጄኔሬተርና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት ክልሉ ሰላምን ከማፅናት አልፎ በልማት ስራ ላይ መሆኑን አቶ አሻድሊ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ተቋርጠው የቆዩ የመንገድ ፕሮጀክቶች እንዲጀምሩ ከፌዴራል መንግስት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመው፤ በክልሉ አቅም የመንገድ እና የድልድይ ግንባታ እየተከናወነ ቢሆንም አሁንም ሰፊ ስራ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።