VAMN – ጥር- 23/2017 ዓ.ም
የብልፅግና ፓርቲ ዛሬ ማካሄድ በጀመረው በ2ኛ መደበኛ ጉባኤው ትላንትን ፣ ዛሬንና ነገን የሚያስተሳስሩ ቀጣይ አቅጣጫዎች ያስቀምጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ አመለከቱ ፡፡
የብልፅግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱን በዓድዋ ድል መታሰቢያ ማካሄድ ጀምሯል፡፡
በጉባኤው ላይ አቶ አደም ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፣ ብልፅግና ፓርቲ ሚዛናዊነትንና አስተሳሳሪ ትርክትን መሰረት በማድረግ በኢትዮጵያ የነበሩ ተቃርኖዎችን የሚያስታርቅና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማስታረቅ የተቋቋመ ፓርቲ መሆኑን አመልክተዋል ፡፡
ይህንን መሻት እውን ለማድረግም ብልፅግና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያለ ልዩነት ያቀፈ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ ሆኖ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስረድተዋል ፡፡
ፓርቲው የዴሞክራሲ ባህልን ማጎልበትና የወንድማማችነትና እህትማማችነት እሴትን ማዳበር ወሳኝ መሆኑን በማመን ይህን እውን ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ይገኛልም ብለዋል፡፡
እንደ ፓርቲ ቃልን በተግባር የመለወጥ ባህልን በመጠቀም የገጠሙትን ፈተናዎች ህዝብን በማሳተፍ መሻገር ችሏልም ነው ያሉት አቶ አደም፡፡
ከእዳ ወደ ምንዳ ለመሸጋገር ጥንካሬና ድክመትን በመለየት እንዲሁም ፈተናን ወደ እድል በመቀየር ለዛሬና ለነገ ትውልድ ጥቅም መረጋገጥ በህልም ጉልበት ለእመርታዊ እድገት በመስራት ለዛሬ ቀን መደረሱንም አመልክተዋል ፡፡
በመጀመሪያው ጉባኤ ለህዝብ ቃል የተገቡ ጉዳዮች ምን ያህል እንደተፈፀሙና በህዝብ እርካታና በሀገራችን ዘላቂ ጥቅሞች አንፃር የተገኙ ድሎችን በመመዘን እንዲሁም የአባላትና የአመራሩን ሁኔታ በጥልቀት በመገምገም ፓርቲያዊ ቁመናው እንደሚመረመርም አመልክተዋል ፡፡
ያለፈው ጊዜ በተገባው ቃል መሰረት በስንዴ ምርት ራስን ከመቻል ባለፈ ለኤክስፖርት መብቃት መቻሉን ፣ በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር 1ኛ በመሆን ክብር መጎናፀፍ የተቻለበት ፣ ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ ያደገበት ፣ የህዳሴ ግድቡን ግንባታ ማገባደድ የተቻለበት እንዲሁም ደረጃቸውን የጠበቁ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማትና የነበሩትን በመጠገንም ዘርፉን በከፍተኛ ደረጃ ማነቃቃት የተቻለበት መሆኑን አብራርተዋል ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በዲጂታል ስትራቴጂ ተቋማት ዘመኑን የዋጁ እንዲሆኑ ማድረግ የተጀመረበት ፣ የማዕድን ዘርፉ ኤክስፖርት በከፍተኛ ደረጃ ያደገበት ፣ ከተሞችን ለኑሮ ምቹና አለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ውጤታማ ስራዎች ማከናወን የተጀመረበት ፣ በርካታ ሰው ተኮር ስራዎች የተሰራበት ፣ የኑሮ ውድነትና የስራ እድል ፈጠራ ስራዎች የተከናወኑበት እና የተወረወሩ ቀስቶችን በብልሀት በማምከን የሀገርን ሉዓላዊነት ማስከበር የተቻለበት እንደነበርም ነው የጠቆሙት፡፡
በሌላም በኩል ተገደን የገባንባቸውን ግጭቶች ለሰላም ያለንን ቁርጠኝነት በሚያረጋግጥ አኳኋን በሆደ ሰፊነት የተቋጨበት ፣ የፅንፈኝነት ሰንኮፍና የዋልታ ረገጦችን አሜኬላ በዘላቂነት መንቀል የሚያስችሉ ውጤታማ ስራዎች የተሰሩበት መሆኑንም አመልክተዋል ፡፡
ከስኬቱ ባለፈ ከኋላ ቀር የፖለቲካ ባህል የድህረ እውነት ዘመን ካመጣቸው አዳዲስ ፈተናዎችና ከአፈፃፀም ልዩነት ጋር በተያያዘ የፀጥታ ፣ የኢኮኖሚ ፣ የፖለቲካና የመልካም አስተዳደር ተግዳሮቶች ማጋጠሙንም አመልክተዋል ፡፡
ያሉ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠልና ድክመቶችን ለማረም እንዲሁም የውስጠ ፓርቲ ጥንካሬን ለማረጋገጥ የሚረዱ ሰፋፊ ስልጠናና ውይይቶች ተካሂደዋል ያሉት ምክትል ፕሬዝደንቱ ፓርቲውን በአሰራር በአደረጃጀትና በፋይናንስ ለማጠናከር የሚረዱ ስራዎች መሰራታቸውም አመልክተዋል ፡፡
በዚህ ጉባኤም ትላንትን ፣ ዛሬንና ነገን የሚያስተሳስሩ ቀጣይ አቅጣጫዎችም ይቀመጣሉ ብለዋል ምክትል ፕሬዝደንቱ ፡፡
በሽመልስ ታደሰ



All reactions:
71Muluken Getnet and 70 others