AMN-ጥር 7/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ብሔራዊ የፍልሰት መረጃ ቋት ለማልማት የፍልሰት መረጃን ከሚያመነጩ ተቋማትጋር የስምምነት ፊርማ ተፈራረመ፡፡
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ብሄራዊ የፍልሰት መረጃ ቋትን ለማልማት ስምምነት የተፈራረመው ከሚመለከታቸው ሌሎች 11 ተቋማት ጋር ነው፡፡
የፍትህ ሚኒስቴር፣ ስራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ሰላም ሚኒስቴር፣ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በስምምነቱ ሥር ተካተዋል፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ 29 ፍልሰት የሚበዛባቸው ዞኖች፣14 የድንበር መውጫ በሮች፣ 135 መተላለፊያ ቦታዎች ያሏት የስደተኞች መነሻ፣ መሸጋገሪያና መዳረሻ ሀገር ነች፡፡
ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ሲዳማ ክልሎች ከፍተኛ ኢ-መደበኛ ፍልሰት ያለባቸው አካባቢዎች መሆናቸውም ተለይቷል፡፡
የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ፍልሰትን ህጋዊ በሆነ መልኩ ማከናወን ከተቻለ ለዜጎች እና ለሀገር ጠቃሚ ነው፡፡
ይሁን እንጂ በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ለመሻገር መሞከር ጉዳቱ ለግለሰቦችም ለሀገርም ይሆናል ብለዋል፡፡
መንግሥት ህገ ወጥ ፍልሰትን በመከላከል ዜጎች በህጋዊ መንገድ ከሀገር ወጥተውና ደህንነታቸው ተጠብቆ መሥራት እንዲችሉ ሁሉን አቀፍ የፍልሰት አስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት የፍልሰት ጥናትና ምርምር ቡድን ተቋቁሞ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
በሰዎች የመነገድና ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፖሊሲ ጀምሮ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011፣ በሰው መነገድና ሰውን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን መከላከልና መቆጣጠር አዋጅ ቁጥር 1178/2012 ስራ ላይ መዋላቸውንም ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኢ-መደበኛ ፍልሰትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ተቋማት ተናበው የሚሰሩበት ወጥ የሆነ የፍልሰት መረጃ ቋት ለማልማት ሥምምነት ተፈርሟል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ በሚደረግ የቤተሰብ ጥናት ውስጥ የፍልሰት መረጃ ለማሰባሰብ ጥረት ሲደረግ እንደነበር አንስተዋል፡፡
ይሁን እንጂ የፍልሰት መረጃን በአግባቡ መሰነድ ከሚኖረው አበርክቶ አንፃር በህዝብና ቤት ቆጠራ እና ናሙና ብቻ ማደራጀት መተንተን በቂ አይደለም ብለዋል፡፡
በመሆኑም ከብሄራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽህፈት ቤት እና ሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ብሄራዊ የፍልሰት መረጃ ቋት ለማልማት ሥምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡
በዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ተልዕኮ ሀላፊ አቢባቶው ዋኔ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ከፍልሰት ጋር በተያያዘ ለምተሰራቸው ስራዎች እገዛ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡
የፍልሰት አስተዳደርን ለማጠናከር የሚደረጉ ትብብሮች ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸው፤ በፍልሰት ዙሪያ ፈጣንና አስተማማኝ መረጃ ለመለዋጥ ያግዛል ብለዋል፡፡
የስደተኞችና ተፈናቃዮችን መረጃ በአግባቡ መሰነድ ተዓማኒነት ያለው አገልግሎት መስጠትና ህይወትን መታደግ የሚያስችል መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ብሔራዊ የፍልሰት መረጃ ቋት ማልማት ለተደረጋው ሥምምነትም ከተቋማት ጋር ያለንን ትብብር ያሳያል ያሉት ሀላፊዋ፤ በቀጣይም በትብብር ለመሥራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡