ብዝሃ አገልግሎት በአንድ መሶብ

You are currently viewing ብዝሃ አገልግሎት በአንድ መሶብ

በሀገራችን የአገልግሎት ክብደትና ዋጋ በተገልጋዩ እርካታ ብቻ የሚለካ ሆኖ ዘመናትን ዘልቋል፤ ‘ደንበኛ ንጎስ ነው’ ይሉት የአበው አባባልም ከዚሁ እሳቤ የሚመነጭ ይመስላል። ነገር ግን በዛሬው ዓለም አገልግሎት ጥልቅ ትርጉም እና ግዙፍ ዋጋ ያለው ጉዳይ ሆኖ እናገኘዋለን።

ስማርት ሲቲስ አይደንቲቲ (Smart Cities Identity) የተሰኘ ገጸ ድር 25 ምርጥ መንግስታዊ ግልጋሎት የሚሰጡ የዓለም ሀገራት በሚል ርዕስ ለንባብ ባበቃው ጽሑፍ፣ ዘመናዊና ቀልጣፋ መንግስታዊ ግልጋሎት የተገልጋይን እርካታ ከማረጋገጥ ያለፈ አንድምታ እንዳለው ያትታል። ዴንማርክ፣ ኤስቶንያ፣ ሲንጋፖር፣ ፊንላንድ እና ዩናይትድ ኪንግደም መንግስታዊ ግልጋሎቶችን በተሻለ ደረጃ ዲጂታላይዝ ከአደረጉ ሀገራት ተርታ ይሰለፋሉ።

ሀገራቱ ግልጋሎቶቻቸውን ዲጂታላይዝ በማድረጋቸው የወረቀትና ተያያዥ ወጪዎችን አስቀርተዋል፤ ምርታማነትን ጨምረዋል፤ የሰራተኞቻቸውን የፈጠራ ችሎታና ክህሎት አሳድገዋል፤ ምቾት እና ውበት ያለው የስራ ከባቢ ፈጥረዋል፤ የተገልጋዮችን ጊዜ ቆጥበዋል፤ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ህዝባዊ የአስተዳደር ስርዓት እውን አድርገዋል። ይህም ከዓመት ዓመት እያደገና እየደረጀ የሚሄድ ኢኮኖሚ እንዲኖራቸው አስችሏል ይላል።

በመረጃው መሰረት በርካታ ሀገራት ለዚህ ጉዳይ ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው ባለመስራታቸው ዋጋ እየከፈሉ ነው። ኢትዮጵያም ከእነዚህ ሀገራት ተርታ እንደምትሰለፍ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተደጋግመው በሚነሱ ቅሬታዎች ማረጋገጥ ይቻላል። ይህም ኢትዮጵያ አብዝታ ከምትፈተንባቸው ጉዳዮች መካከል ኋላ ቀር የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት አንዱ መሆኑን ያመላክታል። ክፍተቱ ነዋሪዎችን ለእንግልት፣ የገንዘብ ወጪና የጊዜ ብክነት ሲዳርግ ቆይቷል። ይሁንና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታላይዝ ለማሸጋገር ሲደረግ በቆየ ጥረት አበረታች ውጤቶች መታየት ጀምረዋል፡፡ ሰሞኑን ተመርቆ ወደ አገልግሎት የገባው ‘መሶብ’ የአንድ መስኮት አገልግሎት ማዕከልም የአገልግሎት አሰጣጡን የበለጠ እንደሚያዘምነውና እንደሚያቀላጥፈው ከወዲሁ ላቀ ያለ ግምት ተሰጥቶታል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት ተመርቆ ወደ አገልግሎት የገባው ‘መሶብ’ የአንድ መስኮት አገልግሎት ማዕከል 12 ተቋማት 40 የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጡበት ይገኛል፡፡ ማዕከሉ የመንግስት አገልግሎቶችን ሪፎርም ለማድረግ በተያዘ አቅጣጫ መሠረት ነው የተተገበረው። ማዕከሉ መንግስታዊ ግልጋግሎቶች በቴክኖሎጂ የታገዙ፣ በአንድ ማዕከል ተሰብስበው እንዲሰጡ በማድረግ የዜጎችን እንግልት ለመቀነስ እና ለሙስና ተጋላጭ የሚያደርጉ አሰራሮችን ለመቀነስ ታስቦ የተተገበረ አገልግሎት ነው ተብሏል፡፡

እስከ አሁን ባሉት ጊዜያት የብሔራዊ መታወቂያ፣ የኢትዮጵያ ፓስታ አገልግሎት፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፣ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት፣ የትምህርት ምዘና ፈተናዎች አገልግሎት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አገልግሎቶች በማዕከሉ ይሰጣሉ፡፡ አንድ ተገልጋይ ለአንድ አገልግሎት በርካታ ቦታ መጓዝ ሳይጠበቅበት በዚህ ማዕከል ብቻ በርካታ አገልግሎቶችን ማግኘት ጀምሯል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ማዕከሉን መርቀው ወደ አገልግሎት ባስገቡበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ የህዝብ ቅሬታ ያሉባቸውን ዘርፎች እስከወዲያኛው  በሚፈታ መንገድ ሪፎርም እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፣ መሶብ የአንድ መስኮት አገልግሎት ማዕከልም በአገልግሎት ዘርፍ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ታልሞ የተጀመረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ማዕከሉን መርቀው ወደ አገልግሎት ባስገቡበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ማዕከሉ የአገልግሎት ዘርፍ ችግሮችን በእጅጉ እንደሚያቃልል ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በማዕከሉ ውስጥ አገልግሎት የሚሰጠው ሶፍትዌር በኢትዮጵያዊያን መሰራቱን ጠቁመው፣ አገልግሎቱን የሚሰጡ ወጣቶችም ዘመኑን በሚመጥን አስተሳሰብ፣ በላቀ የስራ ተነሳሽነትና ፍላጎት እንዲሁም ቴክኖሎጂ ማገልግል በሚችሉበት ልክ የተዘጋጁ ናቸው ብለዋል፡፡

ሌብነት ስርዓት ዘርግተን ስንተገብር ይጠፋል ብለው፣ ይህ ካልሆነ ሰዎች የሚያደርጉትን የሁለትዮሽ ድርድርና ስምምነት በቀላሉ ልንደርስበት አንችልም፡፡ በገቢዎች ምሬት አለ፤ ፓስፖርት ላይ የወረፋ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ይህ ችግር ስርዓት በመዘርጋት እንዲጠፋ ይደረጋል፡፡ መሶብ የአንድ መስኮት አገልግሎት ማዕከል ደግሞ ይህን ችግር ለመቅረፍ አስፈላጊ ነው የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ታች ወዳሉት መንግስታዊ መዋቅሮች ሲወረድ ቢሮ ይዘጋል፤ ስብሰባ ይበዛል፡፡ ሰዎች በቀላሉ አገልግሎት አያገኙም፡፡ ይህን ለመፍታትም መንግስት ቀበሌን ማዘመን እና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ተቋማት ማድረግ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ሲሉ አክለዋል

በሂደት መሶብ የአንድ መስኮት አገልግሎት ማዕከል በሁሉም የክልል ዋና ዋና ከተሞች እና በርከት ያለ ህዝብ የሚኖርባቸው ከተሞች መጀመር አለባቸው፡፡ ይህ ሲሆን ህዝብ የሚረካበት፣ ሌብነት የሚጠፋበት፣ ስራ የሚቀላጠፍበት እንዲሁም ኢንቨስትመንት በፍጥነት የሚያድግበትን አውድ በኢትዮጵያ ውስጥ መፍጠር ይችላል ማለታቸው ይታወሳል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ይህን ስርዓት ለመዘርጋት በመስራት ላይ እንደሚገኝ ባሳለፍነው ሳምንት በተካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ጉዳዩን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የከተማዋ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማም መሶብ የአንድ መስኮት አገልግሎት ማዕከልን በፍጥነት ለማድረስ እየሰራች ነው ያሉት ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች፣ ከተማዋ ከምትሰጣቸው በሺህ ከሚቆጠሩ አገልግሎቶች 87 ዋና ዋና እና 262 ንዑስ የአገልግሎት አይነቶች ዲጂታላይዝ ተደርገዋል፡፡ ዲጂታላይዝ የተደረጉት እነዚህ 347 አገልግሎቶች ወደ አንድ ማዕከል ይመጣሉ ብለዋል፡፡

እንደ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች ማብራሪያ፣ እንደመሶብ አይነት ስርዓቶችን እያሰፉ በመሄድ የአገልግሎቱን ዘርፍ ችግር ለመቅረፍ ይሰራል። ቢሮ ገብቶ አንዳችም ሳይሰሩ ውሎ መውጣት፣ ተገልጋይን አለማክበር፣ የአገልጋይነት እሳቤ ብልሽት፣ የጉቦኝነት ልምምድ፣ አንድ ጊዜ ከተቀጠረ የሚነካ የማይመስለው የመንግስት ሰራተኛ እና ሹመኛ አዝማሚያ መቀየር አለበት፡፡ ተገልጋዩም አመለካከቱ መቀየር አለበት፡፡ የሰው አዕምሮ ሲቀየር፤ ለዚህ አገልግሎት የሚመጥን ባለሙያና አመራር መፍጠርም ይቻላል፡፡

የኮሪደር ልማቱ የአገልግሎት ዘርፉን ለማዘመን የሚያስችሉ የመሠረተ ልማት ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችል ዕድል እየፈጠረ መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች፣ ከፊታችን ያለው ጊዜ ህዝቡ ሮሮ የሚያነሳባቸው የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች እንዲቀረፉ ትልቅ እምነት የተጣለበት ስራ ተጀምሯል። አገልግሎቶች ወደ አንድ ማዕከል እንዲመጡ፣ መናበብ እንዲችሉ እየተደረገ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ማዕከል እየተገነባ ነው ብለዋል፡፡

ለመሆኑ ‘መሶብ’ የአንድ መስኮት አገልግሎት ማዕከል ተጠባቂ ውጤቶች ምንድን ናቸው ስንል የጠየቅናቸው የምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ተንታኝ አቶ ኪሩቤል ሰለሞን፣ ማዕከሉ አገልግሎቶችን በማዘመንና በማቀላጠፍ አይነተ ብዙ ጥቅሞችን ያስገኛል፤ ከሁሉ በላይ ግን በኢኮኖሚው ላይ የሚያመጣው ልዩነት ጉልህ ይሆናል ብለዋል፡፡

ማዕከሉ የኢንቨስትመንት ፍቃድ አሰጣጥ፣ በብድር አቅርቦት፣ በመሠረተ ልማት ዝርጋታና መሰል ጉዳዮች ውስጥ የነበረውን የተወሳሰበ አሰራር በመቅረፍ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት መፋጠን መደላድል ይፈጥራል ሲሉም አክለዋል፡፡

አቶ ኪሩቤል ቀልጣፋና ፍትሐዊ አገልግሎትን ለህብረተሰቡ በአጠረ ጊዜ ውስጥ ተደራሽ ማድረግ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሪፎርምን ተከትሎ ብዙ የውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች ወደ ሀገሪቱ ትኩረት ማድረጋቸውን ገልጸው፣ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ቀላልና ዘመናዊ አሰራርን መከተል አስፈላጊ ነው፡፡ መሶብ የአንድ መስኮት አገልግሎት ማዕከል ደግሞ ይህን ዕድል ይሰጣል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ኪሩቤል ገለጻ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መከተል በሀገሪቱ ውስጥ የቢዝነስ ኢንቨስተሮችን  መስህብን ስለሚጨምር  ኢኮኖሚውን ለማሳደግ  አስፈላጊ ነው፡፡  የግብርና፣ የማዕድን፣ የአቪዬሽን፣ የሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፎችን በተቀላጠፈ አሰራር መንገድ ለመጠቀም እንደሚረዳም ተናግረዋል፡፡

ማዕከሉ ገቢ በተገቢው መንገድ ለመሰብሰብ፣ ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት፣ የተገልጋዮችን እንግልት እና ወጪን በመቀነስ ኢኮኖሚው ላይ የሚኖረው ፋይዳ ዘርፈ ብዙ ነው ብለው፣ አስራ ሁለት የፌዴራል ተቋማት ወደዚህ ማዕከል መግባታቸው ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃም ሊታሰብበት እንደሚገባ መክረዋል፡፡

ከተማዋ የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ ተቋማት መቀመጫ እና የተለያዩ  ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የስበት ማዕከል እንደመሆኗ መጠን ዘመናዊ እና ተወዳዳሪ የአገልግሎት ስርዓትን መዘርጋት ይጠበቅባታል ብለዋል፡፡

በይግለጡ ጓዴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review