AMN-መጋቢት 11/2017 ዓ.ም
‘ኢትዮጵያ “ጥበብና ባህል ለቀጣናዊ ትብብር” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደውን ሁለተኛውን የምስራቅ አፍሪካ የጥበባትና ባህል ፌስቲቫል፣ በውቧ መዲናችንና በግዙፉ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በማስተናገዷ ታላቅ ኩራት ይሰማናል’ ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኀበራዊ ትስስር ገፃቸው ባጋሩት መልዕክት ፣ የተለያዩ ቋንቋዎችን መናገር፣ በልዩ ልዩ ባህሎች ውስጥ ማደግ፣ ከተለያዩ እምነቶች ጋር መኖር – ለእኛ ለአፍሪካውያን ጌጣችን ነው ብለዋል፡፡
“ሥሪታችን ብዝኃነት ነው፡፡ ሕዝቦቻችን፣ ባህሎቻችንና ቋንቋዎቻችን ሰው ሠራሹን ድንበር ይሻገራሉ” ሲሉም ገልጸዋል፡፡

አፍሪካዊት ሀገር ኢትዮጵያም፣ የሰው ዘር መገኛና የኅብረ ባህልና የኅብረ ብሔር ማዕከል መሆኗን ጠቁመዋል፡፡
ሀገራችን በዚህ ዘርፍ ለቀጣናው ሀገራት ትስስር መጠናከር ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክታለችም ብለዋል፡፡ ይህ ደግሞ የባህል ዲፕሎማሲ እና ቀጣናዊ ትሥሥር እንዲጎለብት አስቻይ ሁኔታን ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡
የብዝኃ ባህል ሀብቶች እና የጋራ መገለጫ የሆኑ ዕሴቶችን ለሕዝቦች አንድነትና መግባባት፣ ለልማትና ለዘላቂ ሰላም እንዲሁም ማኅበራዊ ትሥሥርን ለማጎልበት መጠቀም ይኖርብናል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡