
AMN- ግንቦት 13/2017 ዓ.ም
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በጋዛ ሰብአዊ ዕርዳታ ለማከፋፈል መቸገሩን አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ ባለፉት ሁለት ቀናት ሰብአዊ እርዳታ የጫኑ በርካታ ተሸከርካሪዎች ጋዛ ቢደርሱም፣ ሠራተኞቹ እርዳታውን ለህዝቡ ለማድረስ መቸገራቸውን ገልጿል፡፡
እስራኤል በበኩሏ ትናንት ዱቄት፣ የህጻናት ምግብ፣ መድሃኒት እና የህክምና ቁሳቁሶችን የያዙ 93 የጭነት ተሸከርካሪዎች ጋዛ ገብተዋል ስትል ምላሽ ሰጥታለች፡፡
ሀገሪቱ ባሳለፍነው ሳምንት እሁድ ወደ ጋዛ “መሰረታዊ መጠን ያለው” የምግብ እርዳታ እንዲገባ መስማማቷ ይታወሳል፡፡
ወደ ጋዛ ሰብአዊ እርዳታ በአግባቡ እንዲደርስ እስራኤል አስፈላጊውን ትብብር እንድታደርግ ጠንካራ ዓለም አቀፍ ጫና እየተደረገባት ይገኛል፡፡
እንግሊዝ ከሀገሪቱ ጋር ልታደርግ የነበረውን የንግድ ንግግር እስራኤል “በሞራል ረገድ ተቀባይነት የሌለው” ወታደራዊ መስፋፋት በጋዛ እያደረገች ነው በሚል ማራዘሟ ይታወሳል፡፡
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኦረን ማርሞርስቴይን፣ ለእንግሊዝ እርምጃ በሰጡት ምላሽ፣ “የውጭ ጫና እስራኤልን ህልውናዋን ከምትጠብቅበት መንገድ አያወላዳትም” ማለታቸውንም ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል፡፡