ተቋማቱ በቱሪዝም ዘርፍ በትብብር ለመስራት ተፈራረሙ

You are currently viewing ተቋማቱ በቱሪዝም ዘርፍ በትብብር ለመስራት ተፈራረሙ

AMN – የካቲት 25/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ፣ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት እና የቱሪዝም ሚኒስቴር በቱሪዝም ዘርፍ በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ዛሬ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ እና የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ናቸው።

ስምምነቱ የቱሪስቶችን ቆይታ ለማረዘም በሚያስችለው “ስቶፕ ኦቨር ቱሪዝም” ዘርፍ ሲሆን ተጓዦች ከመነሻ አገራቸው በሚነሱበት ጊዜ በመሸጋገሪያነት በኢትዮጵያ ሲያልፉ ጥቂት ቀናት በሀገሪቷ ቆይታ አድርገው ወደ መዳረሻ አገር እንዲሄዱ የሚያስችል የቱሪዝም ዓይነት ነው፡፡

ሶስቱ ተቋማት የተፈራሙት ስምምነት የአዲስ አበባ የቱሪዝም ዕድገትን ለማሳደግ ታሳቢ ያደረገና በከተማዋ የቆይታ ግዜ ለሚኖራቸው መንገደኞች በተዘጋጀ ስቶፕ ኦቨር ፓኬጅ ላይ በጋራ መስራት የሚያስችላቸው ነው።

የመግባቢያ ሰነዱ ዋና ዓላማ አገራችን ለስቶፕ ኦቨር ቱሪዝም ያላትን ሰፊ ዕድል መነሻ በማድረግ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት በተቀናጀ ጥረት ስቶፕ ኦቨር ቱሪዝም እንዲስፋፋ፣ እንዲጎለብት እና ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማሳደግ የሚያስችል የትብብር ማዕቀፍ መዘርጋት መሆኑን ከአየር መንገዱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review