AMN-ጥቅምት 19/2017 ዓ.ም
ተገልጋዩ ማህበረሰብ የሚያነሳቸውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ለመፍታት በልዩ ሁኔታ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ጀማሉ ጀንበር ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ በ2017 የዝግጅት ምዕራፍ ላይ ከለውጥ ስራዎች እና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የክትትል እና ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቋል፡፡
ቢሮው በ59 የማዕከል ተቋማት እና በ11ዱም ክፍለከተሞች የዝግጅት ምዕራፍ ትግበራቸው ላይ ዳሰሳ ማካሄዱን የገለጸ ሲሆን በውጤቱ እና የቀጣይ የትኩረት ስራዎች ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ይገኛል፡፡
መርሐግብሩን ያስጀመሩት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ጀማሩ ጀንበር ፣ የከተማዋን ተቋማት አቅም በመገንባት ከአገልግሎት አሰጣጥ አንፃር ተገልጋዩ በየጊዜው የሚያነሳቸውን ችግሮች በልዩ ሁኔታ ለመፍታት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
ባለፈው በጀት አመት ተገልጋዩ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር፣ የአገልግሎት አሰጣጥ እና ሌብነት እና ብልሹ አሰራር ያለባቸውን ተቋማት ችግሮች ለመፍታት በልዩ ሁኔታ የሪፎርም ስራዎች መከናወናቸውን ኃላፊው አስታውሰዋል፡፡
በዚህም ለውጦች የተመዘገቡ መሆኑን በመጥቀስ በተያዘው በጀት አመትም በትኩረት ሊሰራባቸው የሚገቡ ዘርፎች መኖራቸውን አመላክተዋል፡፡
የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን እና በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ አመራሩ ከፊት ሆኖ መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
የተቋማት የስራ ከባቢ ለሰራተኛ እና ለተገልጋይ ምቹ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
በሩዝሊን ሙሐመድ