ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከደለል ለመጠበቅ የምናከናውናቸውን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የሲቪክ ማህበራት አስታወቁ፡፡
ጽህፈት ቤቱ “አንድ እቅድ አንድ ሪፖርት”ለተቀናጀ የአባይ ተፋሰስ ልማት የሲቪክ ማህበራት ሚና በሚል መሪ ሃሳብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር አድርጓል።
በዚሁ ወቅት የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ከድህነት ለመላቀቅ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳዩበት ትልቅ ሀገራዊ ሀብት መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት 14 ዓመት ህዝብና መንግስት በጋራ በመቆም የህዳሴ ግድቡ ግንባታ ከጫፍ እንዲደርስ ትልቅ ሚና መጫወታቸውን ጠቅሰዋል።
ህዝቡ ለግድቡ ግንባታ በእውቀት ፣በገንዘብ ፣በዲፕሎማሲ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
ግድቡ የሚሰጠው ጠቀሜታ ዘመን እንዲሻገር የሚከናወነው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ የሁሉንም ዜጋ ርብርብ እንደሚፈልግ ነው የገለጹት።
የህዳሴ ግድቡን ከደለል ለመታደግ እንደ ሀገር በሚከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የሲቪክ ማህበራት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

የፒ ኤች ኢትዮጵያ ኮንሰርቲየም ዋና ዳይሬክተር እንዳሻው ሞገሴ፥ ድርጅቱ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ውጤታማ ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የሲቪክ ማህበራት ግድቡ ለደለል እንዳይጋለጥ በአባይ ተፋሰስ የጀመርናቸውን የተፋሰስ ልማት ስራዎች በተቀናጀ መልኩ ለመስራት የሚያስችለንን አቅም መፍጠር አለብን ብለዋል።
የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት የተራቆቱ መሬቶችን ለመጠበቅ ፣የሀገሪቱን የአረንጓዴ ሽፋን ለማሳደግ፣ በአባይ ተፋሰስና በሌሎች አካባቢዎች የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የበኩሉን ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ የተቋሙ ባለሙያ መኮንን አለኸኝ (ዶ/ር) መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ድርጅቱ በአባይ ተፋሰስ ዙሪያ በሚተገበሩ የተቀናጁ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ተገቢውን ተሳትፎ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።