AMN – መጋቢት 11/2017 ዓ.ም
ትምህርት እንዲስፋፋ በቅድመ መደበኛ ትምህርት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በዛሬው እለት የመንግስትን የ6 ወራት እቅድ አፈፃፀም በተመለከተ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡
መንግስት በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ የትምህርት ቤት ጥገናና የማስፋፋት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከመጽሃፍ ሽያጭ ሳይቀር ያገኘነውን ገቢ በአብዛኛው ለትምህርት ቤት ግንባታ እንዲውል አድርገናል ብለዋል፡፡
ሆኖም ግን በየአካባቢው የምንዋጋቸው ሰዎች የድንቁርና ጌቶች በመሆናቸው እና
ትምህርት ምናቸውም ስላልሆነ ትምህርት አትማሩ በማለት ይከለክላሉ፣ ይህ ደግሞ ትምህርት እንዳይስፋፍ እንቅፋት እየሆነ ይገኛል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ይህ ሁኔታ ደግሞ ልጆች እንዳይማሩ ስለሚያደርግ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያመጣ ነው ብለዋል፡፡
ለወደፊትም ከህዝባችን ጋር በመሆን ትምህርት ቤቶችን በተለይም የቅድመ መደበኛ ትምህርትን የማስፋፋቱን ተግባር አጠናክርን የምንቀጥልበት ይሆናል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡