ቦሊቪያ ውስጥ ከትናንት በስቲያ በበረራ ላይ የነበረች አነስተኛ አውሮፕላን ድንገት ከአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች እይታ (ራዳር) ትሰወራለች።
በሰሜን ቦሊቪያ ከባውረስ ወደ ትሪኒዳድ ከተማ በመጓዝ ላይ የነበረችው አውሮፕላኗ ባጋጠማት ድንገተኛ የሞተር እክል ጉዞዋ ተሰናክሎ በፈታኝ ሁኔታ በአማዞን ጫካ ውስጥ በሚገኘው ኢታኖማስ ወንዝ አቅራቢያ ታርፉለች።
በውስጧ የነበሩት 5 ተሳፋሪዎችም አውሮፕላኗ እየተላጋች ካረፈችበት ረግረጋማ ሐይቅ በሞት ሽረት ትግል ተጋግዘው ህይወታቸውን ያድናሉ።
የአውሮፕላኗ ጣሪያ ላይ ወጥተው በነፍስ የሚደርስላቸውን ሰው ሲጠባበቁም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ሐይቁ የግዙፍ አዞዎች መኖሪያ ሆኖ የአዳኝ ታዳኝ ፍልሚያ ይጀመራል።

አዞዎቹ እስከ 3 ሜትር ድረስ እየቀረቧቸው በለስ የቀናቸውን ነጥቀው ለመሄድ መተጋተግ ይይዛሉ።
የ29 ዓመቱ ፓይለት፣ ሦስት ሴቶች እና አንድ ህፃን በጩኸት፣ በማስፈራራት እና በቅርብ የተገኘን ሁሉ በመወርወር 36 ሰዓታት የፈጀ ትንቅንቅ ያደርጋሉ።
በመጨረሻም በአካባቢው ሲያልፉ የነበሩ ዓሳ አጥማጆች ደርሰው እንደታደጓቸው ቢቢሲ ዘግቧል።