የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ በሚታዩ የባህር ማዶ ፊልሞች ላይ የ100 ፐርሰንት ታሪፍ እንደሚጥሉ አስታውቀዋል።
ከዓለም ሀገራት ጋር በከባድ የንግድ ፍልሚያ ላይ የሚገኙት ፕሬዚዳንቱ፣ የሀገሪቱ የንግድ መመሪያ ቀረጡ የሚፈጸምበትን አግባብ እንዲያበጅ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ገልጸዋል።
የአሜሪካ የፊልም ኢንዱስትሪ “በፍጥነት እየሞተ ይገኛል” ያሉት ፕሬዚዳንቱ ለዚህም ሌሎች ሀገራት “ፊልም ሰሪዎችን እና ስቱዲዮ ገንቢዎችን ለመሳብ ድጎማ በመስጠት በቅንጅት እያደረጉት ያለውን ጥረት” በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
የሀገራቱን “የተቀናጀ ጥረት”፣ “የብሔራዊ ደህንነት ስጋት” ሲሉ የገለጹት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ ለዓመታት መቀመጫቸውን በሆሊውድ ያደረጉ ፊልም ሰሪዎች ርካሽ ዋጋ ፍለጋ መዳረሻቸውን ወደ እንግሊዝ እና ካናዳ በማድረግ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ትራምፕ “ትሩዝ ሶሻል” በተሰኘው የማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ “በአሜሪካ ዳግመኛ ፊልሞች ሲሰሩ ማየት እንፈልጋለን” የሚል መልዕክት አጋርተዋል።
መልዕክቱን ተከትሎ የሀገሪቱ የንግድ ሚኒስትር ሃዋርድ ሉትኒክ፣ የታሪፍ ጭማሪውን መልክ ለማስያዝ እየተሰራ መሆኑን መግለጻቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።