ሩሲያ በዩክሬን ላይ ግዙፍ አየር ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ትራምፕ ያስተላለፉት መልዕክት ‘ከልክ በላይ ስሜት የተጫነው’ መሆኑን ክሬምሊን አስታውቋል።
ትራምፕ ከጥቃቱ በኋላ በፑቲን አዕምሮ ላይ ያነጣጠረ ነቀፌታ አዘል መልዕክት ‘ትሩዝ ሶሻል’ በተሰኘው የማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ማስተላለፋቸው ይታወሳል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ የፕሬዚዳንቱ አስተያየት “በጦርነቱ ላይ ሁሉም ሰው ካለው የስሜት ጫና ጋር የተገናኘ ነው” ብለዋል።
ቃል አቀባዩ የአየር ጥቃቱ ዩክሬን በቅርቡ በሩሲያ መሰረተ ልማቶች ላይ ለፈጸመችው ጥቃት የተሰጠ ምላሽ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ሩሲያ ከትናንት በስቲያ በዩክሬን ላይ በፈጸመችው መጠነ ሰፊ የሰው አልባ አውሮፕላን እና የሚሳኤል ጥቃት የ13 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነግሯል።
የአየር ጥቃቱ ያስቆጣቸው ትራምፕ “ፑቲን አንዳች ነገር ሳይነካቸው አልቀረም ፤ የበርካቶችን ህይወት በከንቱ እየቀጠፉ ነው” ማለታቸውን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።