ቻይና ለኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች

You are currently viewing ቻይና ለኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች

AMN-ጥቅምት 19/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ዲጂታል ምጣኔ ሃብት ለመገንባት እያከናወነች ላለው ተግባር ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ቻይና አስታወቀች።

አሊባባ ግሎባል ኢኒሼቲቭ በኤሌክትሮኒክስ ንግድ ዙሪያ ከሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ጋር ውይይት እያደረገ ነው።

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የምጣኔ ሀብትና ንግድ ጉዳይ ሚኒስትር ካውንስለር ያንግ ይሃንግ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ኢትዮጵያ ዲጂታል ምጣኔ ሀብትን ለመገንባት እያከናወነች ያለው ተግባር የሚበረታታ ነው።

ለዚህም ቻይና ኤሌክትሮኒክ ንግድ (E-commerce)ን ጨምሮ ዲጅታል ኢኮኖሚን ለመገንባት በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ለሚገኙ ተግባራት ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አንስተዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ(ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን ለማሳካት፣ በመሰረተ ልማት፣ፖሊሲና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠሯን አስታውሰዋል።

በተመሳሳይ ወጣት ስራ ፈጣሪዎችን በማበረታታት፣የዲጂታል ክህሎትን በማሳደግ እና ትብብርን በማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከአሊባባ ጋር የተፈጠረው ትብብርም ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች ክህሎትን ለማሳደግ፣ልምድ ለመቅሰምና በዓለም አቀፍ ገበያ ተደራሽ በመሆን ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ያግዛል ነው ያሉት።

በአሊባባ ግሎባል ኢኒሼቲቭ ከፍተኛ አማካሪ ዳን ሊዩ በበኩላቸው አሊባባ በደረሰበት የቴክኖሎጂ ደረጃ በአፍሪካ እንዲሁም በኢትዮጵያ የኤሌክሮኒክ ንግድን ለማስፋፋት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

አካታች የንግድ ስርዓትን በዓለም ላይ ለመፍጠር ወጣት ስራ ፈጣሪዎችን በማሰልጠን፣ልምድ በመለዋወጥና ሌሎች ዘርፎች በትብብር እየሰሩ መሆኑንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አሊባባ ግሎባል ኢኒሼቲቭ በኢትዮጵያ ግሎባል አካዳሚውን ለመክፈት ማቀዱንም በመርሃ ግብሩ ላይ ጠቁመዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review