የዩሮፓ ኮንፍረንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ዛሬ ሲከናወን ቼልሲ እና ሪያል ቤቲስ ዋንጫውን ለማንሳት ይፋለማሉ፡፡
በቀጣይ የውድድር ዓመት የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ መሆኑን በፕሪሚየር ሊግ ውጤቱ ያረጋገጠው ቼልሲ ዓመቱን በዋንጫ ለማጠናቀቅ ጥሩ አጋጣሚ ተፈጥሮለታል፡፡
የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ደረጃው ኮንፍረንስ ሊግ ነው ተብሎ ስለማይታሰብ ለፍፃሜ መድረሱ ማንንም አላስገረመም፡፡
ካወጣው ወጪ ፣ ካለው ስብስብ እና ከክለቡ ደረጃ አንፃር ዋንጫውን ቢያነሳም እንደ ስኬት የሚቆጥሩለት ጥቂቶች ናቸው፡፡
አሰልጣኙ ኢንዞ ማሬስካ ግን ለዚህ ሃሳብ ግድ የላቸውም፡፡ ደረጃው ምንም ይሁን ምን ዋንጫው ትልቅ ክብር ይገባዋል ባይ ናቸው፡፡
’’ድል ከቀናን የውድድር ዓመታችን ስኬታማ ነው ብለን በድፍረት መናገር እንችላለን፡፡’’ ሲሉም ተናግረዋል ጣልያናዊው አሰልጣኝ፡፡
ቼልሲ ለዚህ ጨዋታ ሙሉ ቡድኑ ዝግጁ ነው ፤ አዲስ ጉዳት የለባቸውም፡፡በግብ ጠባቂ በኩል የ23 ዓመቱ ዴንማርካዊ ፊሊፕ ዮገንሰን የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ እንደሚካተት አሰልጣኙ ቀድመው አሳውቀዋል፡፡

ማሬስካ ዮርገንሰን ሙሉ ውድድሩን ተጫውቶ ፍፃሜ ደርሷል ፤ ፍፃሜው ላይ ተጠባባቂ ማድረግ ፍትሃዊ አይደለም ብለዋል፡፡
ቼልሲ ዛሬ ካሸነፈ ሰባተኛ የአውሮፓ ውድድር ዋንጫው ይሆናል፡፡ በእንግሊዝ የሚበለጠው ዘጠኝ ዋንጫዎችን ማሸነፍ በቻለው ሊቨርፑል ብቻ ነው።
ሪያል ቤቲስ በአውሮፓ ውድድሮች ላይ ለፍፃሜ ሲበቃ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ የስፔኑ ክለብ በላሊጋው 6ኛ ደረጃ ጨርሶ የዩሮፓ ሊግ ተሳታፊነቱን አረጋግጧል፡፡ ዛሬ ዋንጫ ካነሱ ግን ልዩ ቦታ የሚሰጡት ዕለት ይሆናል፡፡
ምንም እንኳን የማሸነፍ ግምቶች የበዙት ወደ ቼልሲ ቢያጋድሉም ቤቲስ ቀላል ተፎካካሪ አይሆንም፡፡ ፍፃሜ ለመድረስ በነበራቸው ጉዞ ከቼልሲ የበለጠ ፈታኝ ቡድኖችን ገጥመዋል።
የቤቲስ አንጋፋው አሰልጣኝ ማኑኤል ፔሌግሪኒ ክለቡን ተፎካካሪ ያደረጉበት መንገድ እያስወደሳቸው ይገኛል፡፡ቺሊያዊው አሰልጣኝ የዛሬ ተጋጣሚያቸው ቼልሲ አሰልጣኝ ኢንዞ ማሬስካ ጋር በደንብ ይተዋወቃሉ፡፡
ኢንዞ ማሬስካ 2011 ላይ ለማላጋ ሲፈርም አሰልጣኙ ማኑኤል ፔሌግሪኒ ነበሩ፡፡ የተጫዋችነት ጊዜው እንዳበቃ ወደ አሰልጣኝነት እንዲመጣ የገፋፉትም ፔሌግሪኒ ናቸው፡፡
የ71 ዓመቱ አንጋፋ አሰልጣኝ ዌስትሃምን ባሰለጠኑበት ወቅት ረዳታቸው ያደረጉት ኢንዞ ማሬስካን ነበር፡፡ እነዚህ የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው አሰልጣኞች ዛሬ በተቃራኒ ይፋለማሉ፡፡
ጨዋታው ምሽት 4 ሰዓት ይጀምራል፡፡ ፖላንድ በሚገኘው ሮክሎው ስታዲየም የሚከናወነውን ግጥሚያ የቦስኒያ ሄርዞጎቪና ዜግነት ያላቸው ዋና ዳኛ ኢርፋን ፔልይቶ ይመሩታል፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ