ነገ በቻይና ሻንጋይ በሚካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በርካታ ኢትዮጵያውያን ይሳተፋሉ

You are currently viewing ነገ በቻይና ሻንጋይ በሚካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በርካታ ኢትዮጵያውያን ይሳተፋሉ

AMN-ሚያዝያ 24/2017 ዓ.ም

የ2025 የዳይመንድ ሊግ የሁለተኛ ከተማ ውድድር ነገ በቻይና ሻንጋይ ይካሄዳል፡፡ በ5 ሺ ሜትር ወንዶች በሪሁ አረጋዊ ለማሸነፍ ግምት አግኝቷል፡፡ የ2021 እና የባለፈው ዓመት ዳይመንድ ሊግ የርቀቱ አሸናፊ በሪሁ፤ የዚህ ዓመቱን ውድድር ነገ ይከፍታል፡፡

ከፓሪስ ኦሊምፒክ የ10 ሺ ሜትር ብር ሜዳሊያ አሸናፊው በሪሁ አረጋዊ በተጨማሪ ጌትነት ዋለ፣ መዝገቡ ስሜ፣ ኩማ ግርማና አታክልቲ ኪዳኑ እንደሚሳተፉ ይፋ ተደርጓል፡፡

የሴቶች 800 ሜትር ሌላው ኢትዮጵያውያን ለአሸናፊነት የሚጠበቁበት ውድድር ነው፡፡ ጽጌ ድጉማ የማሸነፍ ቀዳሚውን ግምት አግኝታለች፡፡ የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር አሸናፊዋና የፓሪስ ኦሊምፒክ የርቀቱ የብር ሜዳሊያ ባለ ድሏ ጽጌ ከንግስት ጌታቸው፣ ሳሮን በርሄና የርቀቱ ባለ ልምድ ሃብታም ዓለሙ ጋር በመተጋገዝ ሻንጋይ እንደሚያሸንፉ ይጠበቃል፡፡

ቤኒናዊቷ ኖኢል ያሪጎ፣ ኡጋንዳዊቷ ሃሊማህ ናካዪ እንዲሁም አውስትራሊያዊቷ ሳራህ ቢሊንግስ የኢትዮጵያውያን ዋነኛ ተፎካካሪዎች ናቸው፡፡

3 ሺ ሜትር መሰናክል ሌላው የሚጠበቅ ውድድር ነው፡፡ ዚመን ላይ ያሸነፈው ሳሙኤል ፍሬው ለሌላ ድል ነገ ሻንጋይ ይሮጣል፡፡ የወቅቱ የዓለም ቁጥር አራቱ ሳሙኤል ነገ ካሸነፈ መሪነቱን ያሰፋል፡፡ ሳሙኤል ዱጉና፣ ኃይለማሪያም አማረና አብረሃም ስሜ ሌሎች በርቀቱ የሚፎካከሩ አትሌቶች ናቸው፡፡

የኦሊምፒክና ዓለም ሻምፒዮና አሸናፊው ሶፊያን ኢል ባካሊ ሻንጋይ ላይ ለማሸነፍ የሚጠበቅ አትሌት ነው፡፡ ዚመን ላይ በሳሙኤል ፍሬው የተበለጠው ኢል ባካሊ ነገ ወደ ድል ለመመለስ ብርቱ ትግል እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡ ዚመን ላይ ሶስተኛና አራተኛ ሆነው የጨረሱት ኬንያዊያኑ ሲሞን ኪፕሮፕ ኮችና ኤድመንድ ሴሬም ውድድሩን ለማሸነፍ ቀላል ግምት አልተሰጣቸውም፡፡

በታምራት አበራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review