116ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ብሔራዊ የምሥረታ ቀን የማጠቃለያ መርሐ-ግብር ዛሬ በመስቀል አደባባይ ተካሂዷል፡፡
በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) 116 ዓመት መቆየት የራሱ የሆነ ጠቀሜታ ያለው ቢሆንም ቀጣይነት ያለው ሪፎርም እና ስራ ፥ ዘመን የሚዋጅ አቅም መገንባት ካልተቻለ ቁጥር ብቻውን በቂ ሊሆን አይችልም ብለዋል።
ተቋም የሚያድገዉ በእድሉ ሳይሆን በስራ፥ በስልጠና እና በቴክኖሎጂ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ ተቋም ግንባታ በተለይ በሰላም እና ደህነት ተቋማት የተሰራዉ ሪፎርም አመርቂ እንደነበር አንስተዋል፡፡
የተጀመረዉን ለዉጥ ለማስቀጠል ዘመኑን የዋጀ ስልጠና እና ትጥቅ በቀጣይነት ሊኖር እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሳስበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም ከፖሊስ ሰራዊት አባላት የምንጠብቀው የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም፥ ሰላም እና አንድነት በቀጣይነት የማረጋገጥን ስራ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።
130 ሚሊዮን ገደማ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ አንድ መሆን ካልቻለች የግዛት እንድነት እና ብልፅግናን ማረጋገጥ እንደማትችል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
የእኛ አላማ መሆን ያለበት ብሄራዊ ፍላጎቶቻችንን አንጥረን ማወቅ፥ ሰላማችን መጠበቅ፥ ተባብረን መትጋት እንዲሁም ከጎረቤት ህዝቦች ጋር በጋራ መስራት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚያ ያለፈ ነገር ከመጣ ግን እንደአባቶቻችን በአርበኝነት ስሜት የኢትዮጵያን አንድነት እና ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር የሁል ጊዜ ስራችን ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በሊያት ካሳሁን