AMN – የካቲት 25/2017 ዓ.ም
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለዩክሬን የሚደረገውን ወታደራዊ ድጋፍ ማቋረጣቸው ተገልጿል፡፡
የኋይት ሀውስ ባለሥልጣናት ለመገናኛ ብዙሀን በሰጡት መረጃ አሜሪካ ለዩክሬን ታደርግ የነበረውን ወታደራዊ ድጋፍ ያስገኘው መፍትሔ ይኖር እንደሆን በማጤን ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡
አሜሪካ ለዩክሬን ከፍተኛ የጦር መሳሪዎች አቅራቢ ሀገር ስትሆን የዛሬ ሶስት አመት የዩክሬን ሩሲያ ግጭት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ለዩክሬን የጦር መሳሪያዎች እና የፋይናንስ ድጋፍ ስታደርግላት ቆይታለች፡፡
ከሰሞኑ ዶናልድ ትራምፕ እና ዘለንስኪ ዓለምን ግራ ያጋባ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ የዩክሬኑ ፕሬዝዳነት ዘለንስኪ ከሩሲያ ጋር ወደ ሠላም መምጣት ገና እሩቅ ነው ብለው ከተናገሩ ከሰዓታት በኋላ ነው ፕሬዝዳነት ትራምፕ ከውሳኔ የደረሱት ተብሏል፡፡
መሪዎቹ በመካከላቸው እየሰፋ የመጣውን ልዩነት ተከትሎም የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ጦርነቱን ለማስቆም እና የዩክሬንን ሉዓላዊ ክብር ያስጠብቃል ያሉትን ባለ አራት ነጥብ ስምምነት ከፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ጋር አድርገዋል፡፡
ይሁንና አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች ያለ አሜሪካ ተሳትፎ ለሠላም ዋስትና መስጠት ያስቸግራል ማለታቸውን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡
በማሬ ቃጦ