አሜሪካ እና ኢራን የኒውክለር ስምምነት ላይ ለመድረስ መቃረባቸውን ትራምፕ ገለፁ

AMN – ግንቦት 7/2017 ዓ.ም

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በባህረ ሰላጤው ጉብኝታቸው ወቅት አሜሪካ ከኢራን ጋር በኒውክለር ፕሮግራሞቿ ላይ በቀረቡት መደራደሪያዎች ስምምነት ላይ ለመድረስ መቃረባቸውን ተናግረዋል።

ትራምፕ በሁለቱ አገራት መካከል እሁድ ዕለት የተጠናቀቀውን ንግግር ለረዥም ጊዜ ሰላም በሚል፥ በጣም ጠንከር ያለ ድርድር የተደረገበት ሲሉ ገልፀውታል።

ዩናይትድ ስቴትስ ኢራን የኒውክሌር የጦር መሣርያ ማምረት የሚያስችላትን ዩራኒየም ማበልፀግ እንድታቆም ብትፈልግም ኢራን የኒውክለር ፕሮግራሞቿ በአጠቃላይ ለሠላማዊ ተግባራት የሚውሉ መሆናቸውን ትገልፃለች።

በባሕረ ሰላጤው አገራት ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ዶናልድ ትራምፕ በኳታር እንደተናገሩት፣ በኢራን ኒውክለር ፕሮግራም ዙርያ የሚደረገው ድርድር ወደ ስምምነት እየተቃረበ በመሆኑ፣ በቴህራን ኒውክለር ፕሮግራሞች ላይ የሚፈጸመው ወታደራዊ ጥቃት ሊወገድ ይችላል ብለዋል።

የኢራን የጠቅላይ መሪ አያቶላ አሊ ካሜኒ አማካሪ የሆኑት አሊ ሻምካኒ፣ ከአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ አሜሪካ የጣለችውን ማዕቀብ የምታነሳ ከሆነ ኢራን በከፍተኛ ደረጃ የበለፀጉ እና የተከማቹ ዩራኒየሞችን ለመተው ዝግጁ ናት ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

በሊያት ካሳሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review