አምራች ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማሟላት በትብብር መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ

You are currently viewing አምራች ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማሟላት በትብብር መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ

AMN-መጋቢት 1/2017 ዓ.ም

በክህሎት የበቃ የሰው ሃይል ለአንድ ሀገር ምን አስተዋጽኦ ይኖረዋል በሚል ርዕሰ ጉዳይ ጹሁፍ ያቀረቡት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር)፣ የዕድገት ጉዟችንን ለማሳካት የክህሎት ሚና ትልቅ ድርሻ አለው ብለዋል።

‎የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት “ኢትዮጵያ እያሸነፈች ትሻገራለች” በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጀው “ክህሎት ስለ ኢትዮጵያ” ምዕራፍ ሁለት የምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ተግባራዊ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ኢኮኖሚያዊ ስብራትን መጠገን የሚያስችል በርካታ ክህሎት መር ሥራዎች መሰራታቸውንም ዶክተር ተሻለ ገልጸዋል።

‎የቴክኒክና ሙያ ስልጠና በባህሪው ተግባር ተኮር መሆኑን አንስተው፣ በሀገሪቱ በእውቀት፣ በክህሎት እና በአስተሳሰቡ ዝግጁ የሆነ ብቁ የሰው ሀይል ማፍራት ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

‎በተቋማቱ ላይ የሚሰጠውን የዕውቀት ክፍተት ለመሙላት እና የስልጠናን ጥራት ለማምጣት ከኢንዱስትሪዎች ጋር ያለውን ትስስር አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

‎በቴክኒክና ሙያ ተቋማት በአጫጭር ስልጠና ከሶስት ሚሊየን በላይ ዜጎች በመደበኛው ደግሞ ከ500 ሺህ በላይ ዜጎች የሚያልፉ ቢሆንም የክህሎት ልማቱን ከዚህ በላይ ለማሳደግ በትብብር መስራትን እንደሚጠይቅም አንስተዋል፡፡

‎ሌላኛው ጽሁፍ ያቀረቡት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴዔታ ታረቀኝ ቡሉልታ ኢንዱስትሪው የተማረ የሰው ሀይል እንደሚፈልግ ጠቁመዋል።

‎በሀገራችን በርካታ ሥራ አጥ ወጣቶች ቢኖሩም አምራች ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን ክህሎት የሚያሟሉት ጥቂቶች እንደሆኑም ነው የገለፁት።

‎በአምራች ኢንዱስትሪው እና በሥራ አጥ ወጣቶች ችሎታ መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ታረቀኝ፣ ለዚህም ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየሰራ ነው ብለዋል።

‎ክህሎት ግብርናን፣ ቱሪዝምን፣ ማዕድን እና የኢንዱስትሪ ዘርፍን ለማሳደግ ወሳኝ በመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኢንዱስትሪ አቅም ግንባታ ስትራቴጂ ስለመዘጋጀቱ ጠቁመዋል።

‎አሁን ላይ አምራች ኢንዱስትሪው ለሀገር የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከ7 በመቶ እንደማይበልጥ እና ይህም ከውጭ ሀገር በሚገቡ ምርቶች ላይ ጥገኛ መሆናችንን ያሳያል ብለዋል።

ከዚህ ጥገኝነት ለመላቀቅ አምራች ኢንዱስትሪውን መደገፍ እና የሚፈልገውን ችሎታ ማሟላት እንደሚገባም አንስተዋል።

‎አሁን አሁን ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ቢሆንም በቂ ባለመሆኑ በትብብር መስራት ይገባል ብለዋል።

‎በፋሽን ኢንዱስትሪው ላይ ብዙ የቆዩት ወ/ሮ ማህሌት አፈወርቅ ለፋሽን ኢንዱስትሪው ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አንስተዋል።

የሌሎች ሀገራት ተሞክሮም ይህንንኑ ያሳያል ያሉት ወ/ሮ ማህሌት፣ ጊዜውን በሚዋጅ መልኩ ብቁ የሰው ሀይል እና ክህሎት ያለው ዜጋ ማፍራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ለዚህም አስቻይ ሁኔታዎቸ ሊኖሩ እንደሚገባ አመላክተዋል።

በመድረኩ በቀረበ የመነሻ ጽሁፍ ላይም ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።

በሄለን ጀምበሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review