• ጥሪውን ተቀብለው ወደ ከተማ አስተዳደሩ የመጡት አምራቾች እና አቅራቢዎች ቁጥር የሚጠበቀውን ያክል አይደለም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስገንብቶ ለአገልግሎት ካበቃቸው የተለያዩ ፕሮጀክቶች መካከል የግብርና ምርቶች መሸጫ ገበያ ማዕከላት ይጠቀሳሉ፡፡ ይዞታቸውን በመዲናዋ ዋና ዋና የመግቢያ በሮች ላይ በማድረግ የተገነቡት ማዕከላቱ፤ የተቋቋሙት ዓላማም አምራቾችን ከሸማቾች ጋር በቀጥታ በማገናኘት በከተማዋ የሚታየውን የዋጋ ንረትን ማረጋጋት ነው ።
ለማዕከላቱ ግንባታ ከፍተኛ በጀት ወጪ ያደረገው ከተማ አስተዳደሩ፤ የዋጋ ንረትን በዘላቂነት የማረጋጋት ዋና ዓላማ ከማሳካት በተጓዳኝ የአገልግሎታቸውን ዘመናዊነት፣ ምቹነት እና ፍትሃዊነት ለማረጋገጥም ጥረት አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል። በማዕከላቱ ከሚገኙት ደረጃቸውን የጠበቁ እና ዘመናዊ ሱቆች መካከል ቁጥራቸው ከመቶ በላይ የሚሆኑትን በሀገሪቱ ለሚገኙ ለሁሉም ክልሎች እና ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የግብርና ምርት አምራችና አቅራቢዎች ለማስተላለፍ ወስኖ ወደ ተግባር ገብቷል። ከከተማ አስተዳደሩ ለሁሉም ክልሎችና ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በተመሳሳይ የቀረበውን ዕድል ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ቀደም ብለው መጠቀም የጀመሩ ሲሆን፤ በቅርቡ የሲዳማ ክልል በከተማ አስተዳደሩ የተደለደለለትን የመሸጫ ሱቆች ቁልፍ ተረክቧል፡፡
በመዲናዋ ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁ የግብርና ምርቶች መሸጫ ገበያ ማዕከላት ሱቆች በክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለሚገኙ አምራቾች እንዲተላለፍ የተወሰነበትን መነሻ ምክንያት፣ ለሸማቹ እና ለአምራቹ ያለውን ፋይዳ፣ የውሳኔው አተገባበር ወይም አፈፃፀም ሁኔታ እና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ የዝግጅት ክፍላችን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅን አነጋግሯል፡፡
“የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሸማቹን እና አምራቹን ቀጥታ ለማገናኘት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። በከተማዋ አምስቱም የመውጫ እና የመግቢያ በሮች ላይ የገነባቸው እና እየገነባቸው ያሉ የግብርና ምርቶች መሸጫ ገበያ ማዕከላት ከሥራዎቹ መካከል ይጠቀሳሉ” ያሉት ወይዘሮ ሀቢባ፤ ማዕከላቱን ምርት በማቅረብ እና በመሸጥ ከሀገሪቱ ሁሉም ክልሎች እና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሚመጡ አምራቾች እየተጠቀሙባቸው እንደሆነ አንስተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊዋ እንደገለፁት፤ የከተማ አስተዳደሩ የገነባቸውን እና ለአገልግሎት ያበቃቸውን የግብርና ምርቶች መሸጫ ገበያ ማዕከላት የክልል አምራቾች ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ምርታቸውን በማቅረብ እና በመሸጥ እንዲጠቀሙ ለማድረግ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፤ እያደረገም ይገኛል፡፡ አሁን ላይ ማዕከላቱን ምርት በማቅረብ እና ለሸማቹ በመሸጥ የክልል አምራቾች እንዲጠቀሙ ለሁለተኛ ዙር ጥሪ አቅርቦ ለመቀበል እና ለማስተናገድ እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡ ጥሪው ለሁሉም ክልሎች እና ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የቀረበ ሲሆን፤ በመጀመሪያው ዙር ጥሪውን ተቀብለው በመምጣት መስተናገድ የቻሉት ከኦሮሚያ እና ከአማራ ክልሎች የመጡ አምራቾች ናቸው፡፡
ከእነዚህ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የሚመጡ አምራቾች፤ ምርት ማከማቻ እና መሸጫ የሚሆኑ 113 ሱቆችን ለማስረከብ ከተማ አስተዳደሩ ዝግጅቱን አጠናቅቆ መጠባበቅ ከጀመረ ሰነባብቷል። በማዕከላቱ የተዘጋጁት ሱቆች ለተለያዩ የግብርና እና የእንሰሳት ተዋፅኦ ምርቶች ማከማቻነት እና መሸጫነት የሚያገለግሉ ናቸው። በማዕከላቱ ዝግጁ የሆኑት ሱቆች ደረጃቸውን የጠበቁ እና ዘመናዊ ግብዓት የተሟላላቸው እንደየምርቱ ዓይነት፡- ለሰብል፣ ለጥራጥሬ፣ ለአትክልት እና ፍራፍሬ፣ ለወተትና የወተት ተዋፅኦ፣ ለዓሣ ማከማቻና መሸጫ የሚሆኑ ናቸው። የሱቆቹ ድልድል የተደረገው የክልሎቹን እና ከተማ አስተዳደሩን የማምረት እና የማቅረብ አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ በዚሁ መሰረት ሲዳማ ክልል የተደለደሉትን ስድስት ሱቆች ጥር 9 ቀን 2017 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተረክቧል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ በጀት በመመደብ ያስገነባቸውን የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከላት ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች እንዲጠቀሙበት ያመቻቸው ዕድል ሊደነቅ እና ሊመሰገን እንደሚገባው ያነሱት ኃላፊዋ፤ ይህንን ዕድል ከተማ አስተዳደሩ ያመቻቸበት በሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ይህንንም ሲያብራሩ፤ የመጀመሪያው፤ የከተማዋ ነዋሪን የኑሮ ጫና ለማቃለል ነው፡፡ የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከላቱ የተገነቡበት ዋና ዓላማ ነዋሪው ጥራት ያለውን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ የሚሸምትበትን እና የሚጠቀምበትን ሁኔታ ለመፍጠር ነው። ሁለተኛው፤ አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የጋራ ከተማ ወይም መዲና መሆኗን በተግባር ለማረጋገጥ እንደ አንድ ተግባር ለመጠቀም ነው፡፡ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሩ በከተማዋ ተገንብተው ለአገልግሎት በበቁ የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከላት መጠቀም (መገልገል) መቻላቸው፤ ‘አዲስ አበባ የሁላችንም ናት’ የሚለውን ከቃል ባለፈ በተግባር ለማረጋገጥ ስለሚያስችላቸው ነው፡፡
የክልል አምራቾች የማዕከላቱን ሱቆች ለመጠቀም ምን ማሟላት አለባቸው?
የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከላት ሱቆችን ለማግኘት እና ለመጠቀም ከክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የሚመጡ አምራቾች ሦስት መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት እንደሚኖርባቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ጠቁመዋል፡፡ ቅድመ ሁኔታዎቹንም አንድ በአንድ በመጥቀስ አብራርተዋል፡፡
በኃላፊዋ ገለፃ፤ አንደኛው ቅድመ ሁኔታ በማዕከሉ ገብተው ምርታቸውን የሚያቀርቡ እና የሚሸጡ አምራቾች የሚያቀርቡትን ምርት በመደበኛው ገበያ ከሚሸጠው ተመሳሳይ ምርት ዋጋ ከ15 እስከ 20 ከመቶ ቅናሽ አድርገው ለመሸጥ የተስማሙ መሆን አለባቸው፡፡ ይህንን በመፈፀማቸው ለኪሣራ ይዳረጋሉ የሚል ስጋት መኖር የለበትም፡፡ አምራቾቹ ምርታቸውን በማዕከሉ አስገብተው ሲሸጡ ለሚገለገሉበት ሱቅ የሚከፍሉት ኪራይ የለም፡፡ የሚያወጡት ወጪ በማዕከሉ ሲገለገሉ ለሚጠቀሟቸው የውሃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የፅዳት እና መሰል አገልግሎቶች ክፍያ ብቻ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አንድ ሱቅ ለመከራየት የሚጠይቀውን ወጪ በማስላት፤ ወደ ማዕከሉ የሚገቡ አምራቾች ከኪራይ ነፃ፣ እጅግ ዘመናዊና ምቹ በሆነ እና መሠረተ ልማት በመተሟላበት የግብይት ማዕከል ውስጥ ከመደበኛው ገበያ ከ15 እስከ 20 ከመቶ የዋጋ ቅናሽ አድርጎ ለሸማቹ ማህበረሰብ ማቅረብ የጋራ ተጠቃሚነትን (የአምራች እና ሸማች) የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ሁለተኛው ቅድመ ሁኔታ ደግሞ፤ ምርታቸውን በማዕከሉ በሚገኙ ሱቆች ለማቅረብ የሚመጡ አምራቾች የራሳቸው የሆነ የእርሻ ማሣ ያላቸው ስለመሆኑ ሕጋዊ ሰነድ ማያያዝ አለባቸው፡፡ ወይም ምርቱን የሚያመርቱት የእርሻ መሬት ተከራይተው ከሆነ፤ ይህንኑ የሚያረጋግጥ ሕጋዊ ሰነድ ማቅረብ ይኖርባቸዋል። ወይም በኢንቨስተርነት ተሠማርተው እና የእርሻ መሬት ወስደው ለገበያ የሚቀርብ ግብርና ምርት የሚያመርቱ ከሆነ የኢንቨስትመንት ፍቃዳቸውንና የመሥሪያ ቦታቸውን የሚያሳይ ሕጋዊ ሰነድ እና ካርታ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል። እነዚህን አስፈላጊ ሕጋዊ ሰነዶች አሟልተው ማቅረብ ከቻሉ በከተማ አስተዳደሩ ከተዘጋጁት 113 የግብርና ምርቶች መሸጫ ሱቆች መካከል የሚገባቸውን ማግኘት ይችላሉ፡፡
ሦስተኛው ቅደመ ሁኔታ ከምርት አቅርቦት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ቅድመ ሁኔታዎች ያሟሉ የየክልሎች እና ከተማ አስተዳደር አምራቾች፤ ሱቆቹን ለመጠቀም እንዲችሉ ምርታቸውን ያለማቋረጥ ዓመቱን ሙሉ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በማዕከላቱ ባሉ ሱቆች በመጠቀም ምርታቸውን ለማቅረብ እና ለመሸጥ ከገቡ አምራቾች መካከል በጣም ውስን የሆኑት በመሃል እንዳቋረጡ እና ሱቆች እንደተዘጉ ከዚህ በፊት የነበረው ልምድ ያሳያል፡፡ ስለዚህ ምርትን ቢያንስ ውል ከተገባበት ጊዜ አንስቶ ለአንድ ዓመት ያክል ሳያቆራርጡ ማቅረብ ወደ ማዕከላቱ ለመግባት ፍላጎቱ ያለው እና መስፈርቱን የሚያሟላ አካል ግዴታው መሆኑን ማወቅና መፈፀም አለበት፡፡
አምራቾች በተመቻቸው ዕድል ምን ያክል ተጠቀሙ?
ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በማውጣት ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁት ግዙፍ እና ዘመናዊ የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከላት የሚጠበቅባቸውን ወሳኝ ዓላማ እንዲያሳኩ ከተማ አስተዳደሩ የፈፀማቸው ተግባራት እና ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ከአድናቆት አልፎ በምሳሌነት ሊወሰዱ የሚገባቸው ናቸው፡፡ ማዕከላቱ ይዘውት የመጡት ዕድል “በአንድ ድንጋይ ብዙ ወፍ የመምታት” ያክል የሚወሰዱ ናቸው። ማዕከላቱ ለሸማቾች፤ በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራት ያለውን ምርት የሚገዙበትን ሁኔታ ፈጥረዋል። ለአምራቾች፤ ገበያ ላጣው ምርታቸው ሁነኛ የገበያ አማራጭ በሚገኝበት የኢትዮጵያ መዲና ላይ በተገነቡት ዘመናዊና ምቹ የመሸጫ ሱቆች በማቅረብ በብዛት የሚሸጡበትን ወርቃማ ዕድል፤ የሁሉም የጋራ ቤት የሆነችው አዲስ አበባ “ኑልኝ” ብላ ጠርታ እያስተናገደቻቸው መሆኑ ልዩ አጋጣሚ ነው፡፡
በዚህ ተግባር ውስጥ ጎልቶ የሚጠቀሰው ሌላኛው መልካም አጋጣሚ፤ አንድነትንና ህብረትን የሚያጠናክር ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የማስፈን ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ከዚህ ወሳኝ ዕድል እየተጠቀሙ ያሉት የክልል አምራቾች በጣም ጥቂት መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ያስረዳሉ፡፡
የሁሉም የጋራ ቤት የሆነችው አዲስ አበባ ያዘጋጀችውን የግብርና ምርቶች መሸጫ ሱቆች ለክልሎች እና ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለማስተላለፍ የሄደችበትን ርቀትና የመጣውን ውጤት አስመልክቶ የንግድ ቢሮ ኃላፊዋ በሰጡት ማብራሪያ እንዳስረዱት፤ የተወሰነው ውሳኔ ተፈፃሚ እንዲሆን በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አማካኝነት በተፃፈ ደብዳቤ፣ በፌዴራል የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርም በኩል ለሁሉም የክልል እና ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮዎች አሳውቋል፡፡ በጥሪው መሰረት ከላይ የተጠቀሱትን መስፈርቶች የሚያሟሉ አምራችና አቅራቢዎችን ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በመለየት በተሰጣቸው ድርሻ መሰረት መላክ አለባቸው፡፡ ጥሪው ከተደረገ ሁለት ወር አልፎታል፡፡ ይህም ሆኖ ጥሪውን ተቀብለው ወደ ከተማ አስተዳደሩ የመጡት አምራቾች እና አቅራቢዎች ቁጥር የሚጠበቀውን ያክል አይደለም። ለዚህ በምክንያትነት ሊነሳ የሚችለው ጉዳይ በየክልሎቹ ያሉ አምራቾች፤ ስለተፈጠረው ዕድል፣ ከተማዋ ስላላት የንግድ ዕምቅ አቅም… ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ መሆን ነው፡፡
“ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ከተሰጣቸው ድርሻ (ኮታ) ውስጥ 5 ከመቶውን ያክል እንኳን አልተጠቀሙም። በትንሽ ወጪ ነው እንዲገለገሉበት የተዘጋጀው፡፡ ወጪያቸው በካሬ ከ200 ብር ያነሰ ነው” ያሉት ወ/ሮ ሀቢባ፤ “አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለሚገኙ አምራቾች የሚሆን ዕድልን በፍትሃዊነት አመቻችቷል፡፡ በከተማችን ብሎም በሀገራችን ለሚታየው የኑሮ ውድነት ከሚነሱ በርካታ ምክንያቶች አንዱ አምራች እና ሸማች በቀጥታ መገናኘት አለመቻላቸው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በአምራቹ እና ሸማቹ መካከል የሚገቡት ሕገ ወጥ ደላሎች የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ከፍተኛነት ይጠቀሳል፡፡ በከተማ አስተዳደሩ የተመቻቸው የመሸጫ ሱቆችን ለአምራቾች የማስተላለፍ ጅምር፤ ችግሩን ሊያቃልል የሚችል እና የአምራች እና ሸማችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ስለዚህ ዕድሉን በሁሉም ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ፣ አቅሙ ያላቸው እና መስፈርቱን የሚያሟሉ አምራቾች መጠቀም ይችላሉ፤ ይገባቸዋልም፡፡ አምራቾች ይህንን ዕድል ለመጠቀም የሚያስችለውን ቅድመ ሁኔታ እስካሟሉ ድረስ በግልም ሆነ በማህበር ለሚመጡ አምራቾች ከተማ አስተዳደሩ ተገቢውን አገልግሎት ይሰጣል” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በደረጀ ታደሰ